ኦሪት ዘኍልቍ 32
32
ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የተደለደሉት ነገዶች
1ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር የከብት ሀገር እንደ ነበረ አዩ። 2የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም መጥተው ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን፥ የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፦ 3“አጣሮት፥ ዲቦን፥ ያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሌ፥ ሲባማ፥ ናባው፥ ቤያን፤ 4እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች ፊት የሰጣት ምድር የከብት መሰማሪያ ሀገር ናት፤ ለእኛም ለአገልጋዮችህ ብዙ እንስሳት አሉን። 5እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደ ሆነ ይህን ምድር ለአገልጋዮችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ዮርዳኖስን አታሻግረን።”
6ሙሴም ለሮቤል ልጆችና ለጋድ ልጆች አላቸው፥ “ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን? 7እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታጣምማላችሁ? 8ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አድርገው አልነበረምን? 9ወደ ወይን ዘለላ ሸለቆ መጡ፤ ምድሪቱንም አዩአት፤ እግዚአብሔርም ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ መለሱ። 10በዚያም ቀን እግዚአብሔር ተቈጣ፤ እንዲህም ብሎ ማለ፦ 11ከግብፅ የወጡት ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት መልካምንና ክፉን የሚያውቁ ሰዎች እኔን ፈጽመው አልተከተሉምና ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጥ ዘንድ የማልሁባትን ምድር አያዩም፤ 12እግዚአብሔርን ተከትለዋልና ከእነዚህ፥ ልዩ ከሆነ ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር፤ 13እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ በጠና ተቈጣ። በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አንከራተታቸው። 14እነሆም፥ የእግዚአብሔርን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ትጨምሩ ዘንድ እናንተ በኀጢአተኞች ሰዎች በደል በአባቶቻችሁ ፋንታ ተነሥታችኋል። 15እርሱን ትታችሁታልና ዳግመኛም በምድረ በዳ ትታችሁታል፤ በዚችም ማኅበር ሁሉ ላይ ትበድላላችሁ።”
16ወደ እርሱም ቀርበው አሉት፥ “በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶችን፥ ለልጆቻችንም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለጓዛችን” ይላል። ከተሞችን እንሠራለን፤ 17እኛ ግን ለጦርነት ታጥቀን ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ በእስራኤል ልጆች ፊት እንሄዳለን፤ በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ጓዛችን” ይላል። በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ። 18የእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤታችን አንመለስም፤ 19ከዮርዳኖስ ወዲህ ወደ ምሥራቅ ርስታችን ደርሶናልና እኛ ከዮርዳኖስ ማዶ ወደዚያ ከእነርሱም ጋር ርስት አንወርስም።”
20ሙሴም አላቸው፥ “ይህንስ እንዳላችሁት ብታደርጉ፥ ታጥቃችሁም በእግዚአብሔር ፊት ወደ ጦርነት ብትሄዱ፥ 21እርሱም ጠላቱ ከፊቱ እስኪጠፋ ድረስ#“ጠላቱ እስኪጠፋ” የሚለው በግእዝ የለም። ከእናንተ እያንዳንዱ ሰው የጦር መሣሪያውን ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥ 22ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ#“ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ” የሚለው በግእዝ የለም። ከዚያም በኋላ ትመለሳላችሁ፤ በእግዚአብሔርም ፊት በእስራኤል ዘንድ ንጹሓን ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ርስት ትሆናችኋለች። 23እንዲህ ባታደርጉ ግን፥ በእግዚአብሔር ፊት ትበድላላችሁ፤ ክፉ ነገር ባገኛችሁ ጊዜ በደላችሁን ታውቃላችሁ። 24ለልጆቻችሁ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለጓዛችሁ” ይላል። ከተሞችን፥ ለበጎቻችሁም በረቶችን ሥሩ፤ ከአፋችሁም የወጣውን ነገር አድርጉ።”
25የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም ሙሴን እንዲህ ብለው ተናገሩት፥ “እኛ አገልጋዮችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን። 26ልጆቻችን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ጓዛችን” ይላል። ሚስቶቻችንም፥ እንሰሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤ 27እኛ አገልጋዮችህ ግን ሁላችን የጦር መሣሪያችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት እንሄዳለን።”
28ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን፥ የነዌንም ልጅ ኢያሱን፥ የእስራኤልንም ነገድ አባቶች አለቆች አዘዛቸው። 29ሙሴም፥ “የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆች ሁላቸው የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለጦርነት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ። 30የጦር መሣሪያቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ወደ ጦርነት ባይሻገሩ ግን ልጆቻቸውን፥ ሚስቶቻቸውን፥ ከብቶቻቸውንም በፊታችሁ ወደ ከነዓን ምድር ንዱአቸው፤ በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ” አላቸው።#“በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ አላቸው” የሚለው በግእዝ የለም። 31የሮቤል ልጆችና የጋድ ልጆችም መልሰው፥ “ጌታችን ለእኛ ለአገልጋዮችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን። 32የጦር መሣሪያችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፤ ከዮርዳኖስም ማዶ የወረስነው ርስት ይሆንልናል” አሉት።
33ሙሴም ለጋድ ልጆችና ለሮቤል ልጆች፥ ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞሬዎናውያንን ንጉሥ የሴዎንን መንግሥት፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን መንግሥት፥ ምድሪቱንም፥ ከተራሮችም ጋር ከተሞችን፥ በዙሪያቸውም ያሉትን የምድሪቱን ከተሞች ሰጣቸው። 34የጋድ ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን፤ 35ሶፋንን፥ ኢያዜርን፥ 36ናምራን፥ ቤታራንን ሰባት የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ አስረዘሙአቸውም፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ። 37የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፥ ኤልያሌንን፥ ቂርያታይምን፤ በቅጥር የተከበቡ በኤልሜዎንንና፥ ሴባማን ሠሩ፤ 38እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በየስማቸው ጠሩአቸው። 39የምናሴም ልጅ የማኪር ልጅ ወደ ገለዓድ ሄዶ ገለዓድን ያዘ፤ በእርስዋም የነበሩትን አሞሬዎናውያንን አጠፋ። 40ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠው፤ በእርስዋም ተቀመጠ። 41የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮችዋን ወሰደ፤ የኢያዕርም መንደሮች ብሎ ጠራቸው። 42ናባውም ሄዶ ቄናትንም፥ መንደሮችዋንም ወሰደ፤ በስሙም ናቦት ብሎ ጠራቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 32: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in