YouVersion Logo
Search Icon

የማ​ቴ​ዎስ ወን​ጌል 4

4
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መፈተን
(ማር. 1፥12-13ሉቃ. 4፥1-13)
1ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። 2አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ። 3ፈታኝም ቀርቦ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል!” አለው። 4እርሱም መልሶ “ ‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” አለው። 5ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ
6“ ‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤
እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል’
ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር” አለው። 7ኢየሱስም “ ‘ጌታን አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው። 8ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፤ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ 9“ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። 10ያን ጊዜ ኢየሱስ “ሂድ፤ አንተ ሰይጣን ‘ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” አለው። 11ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፤ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር።
ጌታችን የማስተማር ሥራውን እንደጀመረ
(ማር. 1፥14-15ሉቃ. 4፥14-15)
12ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ። 13ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። 14በነቢዩም በኢሳይያስ እንዲህ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ፤
15ምድርና የንፍታሌም ምድር፥
የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤
16ቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤
በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው።”
17ከዚያ ዘመን ጀምሮኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ ይሰብክ ጀመር።
አራቱ ዓሣ አጥማጆች እንደተጠሩ
(ማር. 1፥16-20ሉቃ. 5፥1-11)
18በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። 19እርሱም “በኋላዬ ኑ፤ ሰዎችንም አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ” አላቸው። 20ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። 21ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም። 22እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።
ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን እንደፈወሰ
(ሉቃ. 6፥17-19)
23ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር። 24ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፤ ፈወሳቸውም። 25ከገሊላም ከዐሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in