የሉቃስ ወንጌል 10
10
ሌሎች ሰባ ሰዎችን ስለ መምረጡ
1ከዚህም በኋላ ጌታችን ሌሎች ሰባ ሰዎችን መረጠ፤#በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “አርአየ” ይላል። ሁለት ሁለት አድርጎም ሊሄድበት ወደ አለው ከተማና መንደር በፊቱ ላካቸው። 2#ማቴ. 9፥37-38። ጌታችን ኢየሱስም አላቸው፥ “መከሩ ብዙ ነው፤ ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው፤ እንግዲህ ለመከሩ ሠራተኛ ጨምሮ ይልክ ዘንድ ባለ መከሩን ለምኑት። 3#ማቴ. 10፥16። ሂዱ፤ እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። 4#ማቴ. 10፥7-14፤ ማር. 6፥8-11፤ ሉቃ. 9፥3-5። ከረጢትም፥ ስልቻም፥ ጫማም፥ ምንም ምን አትያዙ፤ በመንገድም ማንንም ሰላም አትበሉ። 5ወደ ገባችሁበት ቤትም አስቀድማችሁ ‘ለዚህ ቤት ሰዎች ሰላም ይሁን’ በሉ። 6በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር ሰላማችሁ ያድርበታል፤ ያለዚያ ግን ሰላማችሁ ይመለስላችኋል። 7#1ቆሮ. 9፥14፤ 1ጢሞ. 5፥18። በዚያም ቤት ተቀመጡ፤ ከእነርሱ የተገኘውንም ብሉ፥ ጠጡም፤ ለሠራተኛ ዋጋው ይገባዋልና፤ ከቤትም ወደ ቤት አትሂዱ። 8ወደ ማናቸውም ከተማ ብትገቡ፥ የዚያ ከተማ ሰዎችም ቢቀበሉአችሁ ያቀረቡላችሁን ብሉ። 9በውስጥዋ የሚገኙትን ድውያንንም ፈውሱ፤ ‘የእግዚአብሔርም መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች’ በሉአቸው። 10ነገር ግን ወደ ማናቸውም ከተማ ብትገቡ፥ የዚያች ከተማ ሰዎችም ባይቀበሉአችሁ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።#“የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ” የሚለው በግሪኩ የለም። እንዲህም በሉ፦ 11#የሐዋ. 13፥51። ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን ዕወቁ። 12#ዘፍ. 19፥24-28፤ ማቴ. 11፥24፤ 10፥15። በፍርድ ቀን ሰዶም ከዚያች ከተማ ይልቅ እንደምትሻል ይቅርታንም እንደምታገኝ እነግራችኋለሁ።
13 #
ኢሳ. 23፥1-8፤ ሕዝ. 26፥1—28፥26፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞ. 1፥9-10፤ ዘካ. 9፥2-4። “ኮራዚ ወዮልሽ! ቤተ ሳይዳ ወዮልሽ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ቀድሞ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው በተቀመጡ ንስሓም በገቡ ነበር። 14ነገር ግን ጢሮስና ሲዶና ከእናንተ ይልቅ በፍርድ ቀን ይቅርታን ያገኛሉ። 15#ኢሳ. 14፥13-15። አንቺም ቅፍርናሆም እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወርጃለሽ።
16 #
ማቴ. 10፥40፤ ማር. 9፥37፤ ሉቃ. 9፥48፤ ዮሐ. 13፥20። “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተንም እንቢ የሚል እኔን እንቢ ይላል፤ እኔንም እንቢ የሚል የላከኝን እንቢ ይላል፤ እኔንም የሚሰማ የላከኝን ይሰማል።”#“እኔን የሚሰማኝ የላከኝን ይሰማል” የሚለው በግሪኩ እና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ አይገኝም።
ስለ ሰባው መልእክተኞች መመለስ
17እነዚያም ሰባው ደስ ብሎአቸው ተመለሱና፥ “አቤቱ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዙልን” አሉት። 18እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ሰይጣንን ከሰማይ እንደ መብረቅ ሲወድቅ አየሁት። 19#መዝ. 90፥13። እነሆ፥ ጊንጦችንና እባቦችን፥ የጠላትንም ኀይል ሁሉ ትረግጡ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠኋችሁ፤ የሚጐዳችሁም ነገር የለም። 20ነገር ግን አጋንንት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ግን ስማችሁ በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ።”
21በዚያች ሰዓትም ጌታችን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ደስ አለው፤ እንዲህም አለ፥ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከዐዋቂዎችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥኸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲሁ ሆኖአልና። 22#ዮሐ. 3፥35፤ 10፥15። ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጠኝ፤ ወልድ ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፤ አብም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር የሚያውቅ የለም። ወልድ ግን ለወደደው ይገልጥለታል።”
23ተመልሶም ደቀ መዛሙርቱን ለብቻቸው አድርጎ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው። 24ብዙ ነቢያትና ነገሥታት እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ተመኙ፤ አላዩምም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኙ፥ አልሰሙም።”
ጌታን ስለ ፈተነው ሕግ ዐዋቂ
25 #
ማቴ. 22፥35-40፤ ማር. 12፥28-34። ከዚህ በኋላ አንድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈትነው ተነሣና፥ “መምህር ሆይ፥ የዘለዓለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” አለው። 26እርሱም፥ “በኦሪት ምን ተጽፎአል? እንዴትስ ታነብባለህ?” አለው። 27#ዘሌ. 19፥18፤ ዘዳ. 6፥5። እርሱም መልሶ፥ “እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ሰውነትህ፥ በፍጹም ኀይልህ፥ በፍጹም ዐሳብህ ውደደው፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል” አለው። 28#ዘሌ. 18፥5። ጌታችን ኢየሱስም፥ “መልካም መልሰሃል፤ እንዲሁ አድርግ፤ ትድናለህም” አለው።
29ራሱን ሊያከብር ባልንጀራውንም ሊንቅ#ግሪኩ እና አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ባልንጀራውን ሊንቅ” የሚለውን አይጽፉም። ወድዶ፥ “ባልንጀራዬ ማነው?” አለው።
ስለ ደጉ ሳምራዊ
30ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይወርድ ነበር፤ ሽፍቶችም አገኙት፤ ደበደቡት፥ አቈሰሉት፥ ልብሱንም ገፍፈው፤ በሕይወትና በሞት መካከል ጥለውት ሄዱ። 31አንድ ካህንም በዚያች መንገድ ሲወርድ ድንገት አገኘው፤ አይቶም አልፎት ሄደ። 32እንዲሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ ቦታ አገኘውና፥ አይቶ እንደ ፊተኛው አልፎት ሄደ። 33አንድ ሳምራዊ ግን በዚያች መንገድ ሲሄድ አገኘው፤ አይቶም አዘነለት። 34#2ዜ.መ. 28፥15። ወደ እርሱም ቀረበ፤ ቍስሉንም አጋጥሞ አሰረለት፤ በቍስሉ ላይም ወይንና ዘይት ጨመረለት፤ በአህያውም ላይ አስቀምጦ እንዲፈውሰው የእንግዶችን ቤት ወደሚጠብቀው ወሰደው፤ የሚድንበትንም ዐሰበ። 35በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለእንግዳ ቤት ጠባቂው ሰጠውና፦ ‘በዚህ አስታምልኝ፤ ከዚህ የሚበልጥ ለእርሱ የምታወጣው ቢኖር እኔ በተመለስሁ ጊዜ እከፍልሃለሁ’ አለው። 36እንግዲህ ሽፍቶች ለደበደቡት ሰው ከእነዚህ ከሦስቱ ባልንጀራ የሚሆነው ማንኛው ይመስልሃል?” 37እርሱም“ምሕረት ያደረገለት ነዋ” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እንኪያስ አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።
ስለ ማርያምና ስለ ማርታ
38ከዚህም በኋላ ሄደው ወደ አንዲት መንደር ገቡ፤ ማርታ የምትባል አንዲት ሴትም በቤቷ ተቀበለችው። 39#ዮሐ. 11፥1። ማርያም የምትባል እኅትም ነበረቻት፤ እርስዋም ከጌታችን ኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ትምህርቱን ትሰማ ነበር። 40ማርታ ግን ብዙ በማዘጋጀት ትደክም ነበር፤ ቆማም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እኅቴ ትታኝ ብቻዬን ስሠራ አያሳዝንህምን? ርጃት በላት” አለችው። 41ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት፥ “ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትደክሚያለሽ፥ ትቸገሪያለሽም፤ ታዘጋጂያለሽም። 42ጥቂት ይበቃል፤ ያም ባይሆን አንድ ይበቃል፤ ማርያምስ የማይቀሙአትን መልካም ዕድል መረጠች።”
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 10: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in