የዮሐንስ ወንጌል 19
19
አይሁድ ጌታን እንደ ገረፉትና እንደ ተዘባበቱበት
1ከዚህም በኋላ ጲላጦስ ጌታችን ኢየሱስን ይዞ ገረፈው። 2ጭፍሮችም የእሾህ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ ደፉበት፤ የቀይ ሐር መጐናጸፊያም አለበሱት። 3ወደ እርሱም እየመጡ፥ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን” ይሉት ነበር፤ በጥፊም ይመቱት ነበር። 4ጲላጦስም እንደገና ወደ ውጭ ወጣና፥ “እነሆ፥ በእርሱ ላይ አንዲት በደል ስንኳን ያገኘሁበት እንደሌለ ታውቁ ዘንድ ወደ ውጭ አወጣላችኋለሁ” አላቸው። 5ጌታችን ኢየሱስም የእሾህ አክሊል ደፍቶ፥ የቀይ ሐር መጐናጸፊያም ለብሶ ወደ ውጭ ወጣ፤ ጲላጦስም፥ “እነሆ፥ ሰውዬው” አላቸው። 6ሊቃነ ካህናትና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ፥ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ፤ ጲላጦስም፥ “እናንተ ራሳችሁ ውሰዱና ስቀሉት፤ እኔስ በእርሱ ላይ በደል አላገኘሁበትም” አላቸው። 7አይሁድም መልሰው፥ “እኛ ሕግ አለን፤ እንደ ሕጋችንም ሊሞት ይገባል፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአልና” አሉት። 8ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ እጅግ ፈራ።
ጲላጦስ ዳግመኛ እንደ መረመረው
9ደግሞም ወደ ፍርድ አደባባይ ገባና ጌታችን ኢየሱስን፥ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። 10ጲላጦስም፥ “ለእኔም አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንደ አለኝ፥ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ፥ አታውቅምን?” አለው። 11ጌታችን ኢየሱስም፥ “ከሰማይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው ታላቅ ኀጢኣት አለበት” አለው። 12ስለዚህም ጲላጦስ ሊፈታው ወድዶ ነበር፤ አይሁድ ግን፥ “ይህን ከፈታኸው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ በቄሣር ላይ የሚያምፅ ነውና” ብለው ጮሁ።
ጲላጦስ ወደ ሊቶስጥሮስ እንደ አወጣው
13ጲላጦስም ይህን ሰምቶ ጌታችን ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ በዕብራይስጥም ገበታ ተብሎ በሚጠራው “ጸፍጸፍ” በሚሉት ቦታ ላይ በወንበር ተቀመጠ። 14የፋሲካም የመዘጋጀት ቀን ነበር፤ ጊዜዉም ስድስት ሰዓት ያህል ነበር፤ ጲላጦስም አይሁድን፥ “እነሆ፥ ንጉሣችሁ” አላቸው፤ 15እነርሱ ግን፥ “አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮሁ። ጲላጦስም፥ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አላቸው፤ ሊቃነ ካህናቱም፥ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱ።
ጌታችን ስለ መሰቀሉ
16ከዚህ በኋላ ሊሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ጌታችን ኢየሱስንም ተቀብለው ወሰዱት። 17መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ። 18በዚያም ሰቀሉት፤ ከእርሱም ጋር አንዱን በቀኝ፥ አንዱንም በግራ አድርገው ሌሎች ሁለት ወንበዴዎችን ሰቀሉ፤ ኢየሱስንም በመካከላቸው ሰቀሉ። 19ጲላጦስም ጽሕፈት ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረ፤ ጽሕፈቱም፥ “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ነበር። 20ከአይሁድም ይህቺን ጽሕፈት ያነበብዋት ብዙዎች ነበሩ፤ ጌታችን ኢየሱስን የሰቀሉበት ቦታ ለከተማ ቅርብ ነበርና፤ ጽሕፈቱም የተጻፈው በዕብራይስጥ፥ በሮማይስጥና በግሪክ ነበር። 21ሊቃነ ካህናትም ጲላጦስን አሉት፥ “እርሱ ራሱ ‘እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ።” 22ጲላጦስም፥ “የጻፍሁትን ጻፍሁ” ብሎ መለሰላቸው።
ልብሱን እንደ ተካፈሉ
23ጭፍሮችም ጌታችን ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ከጭፍሮቹ ለእያንዳንዱ አራት ክፍል አድርገው መደቡት፤ ቀሚሱንም ወሰዱ፤ ቀሚሱም ከላይ ጀምሮ የተሠራ ሥረወጥ እንጂ የተሰፋ አልነበረም። 24#መዝ. 21፥18። እርስ በርሳቸውም፥ “ዕጣ እንጣጣልና ለደረሰ ይድረሰው እንጂ አንቅደደው ተባባሉ፤” ይህም “ልብሶችን ለራሳቸው ተካፈሉ፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፤ ጭፍሮችም እንዲሁ አደረጉ።
ጌታ እናቱን ለደቀ መዝሙሩ አደራ ስለ መስጠቱ
25በጌታችን በኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊት ማርያምም ቆመው ነበር። 26ጌታችን ኢየሱስም እናቱንና የሚወደውን ደቀ መዝሙሩን ቆመው ባያቸው ጊዜ እናቱን፥ “አንች ሆይ፥ እነሆ፥ ልጅሽ” አላት። 27ከዚህም በኋላ ደቀ መዝሙሩን፥ “እናትህ እነኋት” አለው፤ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ተቀብሎ ወደ ቤቱ ወሰዳት።
ስለ ጌታችን ሞት
28 #
መዝ. 68፥21፤ 21፥15። ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ሁሉ እንደ ተፈጸመ ባየ ጊዜ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ “ተጠማሁ” አለ። 29በዚያም ሆምጣጤ የመላበት ማሰሮ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በስምዛ ዘንግ ከአፉ አገናኝተው ጨመቁት።#“ጨመቁት” የሚለው በግሪኩ የለም። 30ጌታችን ኢየሱስም ሆምጣጤውን ቀምሶ፥ “ሁሉ ተፈጸመ” አለ፤ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ።
ከመስቀል ስለ መውረዱ
31አይሁድ ግን የመዘጋጀት ቀን ነበርና፥ የዚያች ሰንበትም ቀን ታላቅ ናትና “ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ አይደር” አሉ፤ ጭን ጭናቸውንም ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት። 32ጭፍሮችም መጥተው ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትን የአንደኛውንና የሁለተኛውን ጭኖች ሰበሩ። 33ወደ ጌታችን ኢየሱስም ሄደው ፈጽሞ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ጭኑን አልሰበሩም። 34ነገር ግን ከጭፍሮቹ አንዱ የቀኝ#በግሪኩ “ቀኝ” አይልም። ጎኑን በጦር ወጋው፤ ያንጊዜም ከእርሱ ደምና ውኃ ወጣ። 35ያየውም መሰከረ፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እርሱም እናንተ ልታምኑ እውነት እንደሚናገር ያውቃል። 36#ዘፀ. 12፥46፤ ዘኍ. 9፥12፤ መዝ. 33፥20፤ ዘካ. 11፥10፤ ራእ. 1፥7። ይህ ሁሉ የሆነው “ከእርሱ ዐፅሙን አትስበሩ” ያለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው። 37ሌላዉም መጽሐፍ ደግሞ“ የወጉትን ያዩታል” ይላል።
ወደ መቃብር ስለ መውረዱ
38ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለፈራ በስውር የጌታችን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረው የአርማትያስ ሰው ዮሴፍ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ይወስድ ዘንድ ጲላጦስን ለመነው፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። እርሱም ሄዶ የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ። 39#ዮሐ. 3፥1-2። ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀብሩበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ። 40እንደ አይሁድ አገናነዝ ሥርዐትም የጌታችን የኢየሱስን ሥጋ ወስደው ከሽቱ ጋር በበፍታ ገነዙት። 41በዚያም በተሰቀለበት ቦታ የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በዚያ የአትክልት ስፍራ ውስጥም በውስጡ ሰው ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር። 42ጌታችን ኢየሱስንም በዚያ ቀበሩት፤ ለአይሁድ የመሰናዳት ቀን ነበርና፤ መቃብሩም ለሰቀሉበት ቦታ ቅርብ ነበር።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 19: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in