ትንቢተ ኤርምያስ 29
29
ኤርምያስ በባቢሎን ለሚኖሩ አይሁድ የላከው ደብዳቤ
1ነቢዩ ኤርምያስ ወደ ተረፉት የምርኮ ሽማግሌዎች፥ ወደ ካህናቱም፥ ወደ ሐሰተኞች ነቢያቱም፥ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ወዳፈለሰውም ሕዝብ ሁሉ ከኢየሩሳሌም የላከው የደብዳቤው ቃል ይህ ነው። 2ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያንና እቴጌዪቱ፥ ጃንደረቦቹም፥ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም አለቆች#“የይሁዳና የኢየሩሳሌም አለቆች” የሚለው በግሪኩ የለም። ነጻዎችና#“ነፃዎችና” የሚለው በዕብ. የለም። እሥረኞች፥ ብልሃተኞችና ብረት ሠራተኞችም#“ብረት ሰራተኞችም” የሚለው በዕብ. ብቻ። ከኢየሩሳሌም ከወጡ በኋላ ነው። 3ኤርምያስም የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር ወደ ባቢሎን በላካቸው በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ደብዳቤውን እንዲህ ሲል ላከው፦ 4የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረክኋቸው ምርኮኞች ሁሉ እንዲህ ይላል፦ 5“ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አታክልትም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ፤ ተጋቡ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ውለዱ፤ 6ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁንም አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ከዚያም ተባዙ፤ ጥቂቶችም አትሁኑ። 7በእርስዋ ሰላም፥ ሰላም ይሆንላችኋልና ወደ እርስዋ ላስማረክኋችሁ ሀገር ሰላምን ፈልጉ፥ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ።”
8የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “በመካከላችሁ ያሉት የሐሰት ነቢያቶቻችሁና ምዋርተኞቻችሁ አያታልሉአችሁ፤ ሕልም አላሚዎች አለምንላችሁ የሚሉአችሁን አትስሙ፥ 9በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና፤ እኔም አልላክኋቸውም፥” ይላል እግዚአብሔር። 10እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰባው ዓመት በባቢሎን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፥ ወደዚህም ስፍራ እመልሳችሁ ዘንድ መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ። 11ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ#“ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ” የሚለው በዕብ. ብቻ። የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። 12እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ሄዳችሁም ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ። 13እናንተ ትሹኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ። 14እገለጥላችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፤ ከአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እናንተንም ከበተንሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።#ምዕ. 29 ቍ. 14 በግሪኩ አጭር ነው።
15“እናንተም፦ እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያትን አስነሥቶልናል ብላችኋልና፤ 16እግዚአብሔር በዳዊት ዙፋን ስለ ተቀመጠ ንጉሥ፥ ከእናንተም ጋር ስላልተማረኩት ወንድሞቻችሁ፥ በዚህች ከተማ ስለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ይላልና፦ 17የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሰይፍንና ራብን፥ ቸነፈርንም እሰድድባቸዋለሁ፤ ከመጐምዘዙም የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉ በለስ አደርጋቸዋለሁ። 18በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም አሳድዳቸዋለሁ፤ ባሳደድሁባቸውም አሕዛብ ሁሉ ዘንድ ለርግማንና ለጥፋት፥ ለማፍዋጫም፥ ለመሰደቢያም እንዲሆኑ በምድር መንግሥታት ሁሉ ዘንድ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 19ይህም የሆነው ቃሌን ስላልሰሙ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በማለዳ ባሪያዎችን ነቢያትን ወደ እነርሱ ሰድጃለሁና፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም፤ ይላል እግዚአብሔር። 20ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።”#ምዕ. 29 ከቍ. 16 እስከ 20 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
21የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚናገሩላችሁ ስለ ቆልያ ልጅ፥#“በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ስለሚናገሩላችሁ ስለ ቆልያ ልጅ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ስለ አክዓብና ሰለ ማሴው ልጅ ስለ ሴዴቅያስ#“ስለ ማሴው ልጅ ስለ ሴዴቅያስ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እንዲህ ይላል፥ “እነሆ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ በዐይኖቻችሁም ፊት ይገድላቸዋል። 22ከእነርሱም የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፦ የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ እግዚአብሔር ያድርግህ የምትባል ርግማንን ያነሣሉ፤ 23በእስራኤል ዘንድ ክፉ አድርገዋልና፥ ከባልንጀሮቻቸውም ሚስቶች ጋር አመንዝረዋልና፥ ያላዘዝኋቸውንም ቃል በስሜ በሐሰት ተናግረዋልና። እኔም አውቃለሁ፤ ምስክርም ነኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።”
24ለአሔልማዊው ለሸማያ እንዲህ በል፦ 25“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌም ወደ አለው ሕዝብ ሁሉ፥ ወደ ካህኑም ወደ ማሴው ልጅ ወደ ሶፎንያስ፥ ወደ ካህናቱም ሁሉ ደብዳቤዎችን በስሜ#ዕብ. “በስምህ” ይላል። እንዲህ ስትል ልከሃል፦ 26ትንቢት የሚናገረውን ሰው ሁሉ፥ የሚለፈልፈውንም ሰው ሁሉ በግዞት ታኖረውና በፈሳሽም ታሰጥመው ዘንድ በእግዚአብሔር ቤት አለቃ እንድትሆን እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ፋንታ ካህን አድርጎሃል። 27አሁንስ ትንቢት ተናጋሪውን የአናቶቱን ሰው ኤርምያስን ስለ ምን አትዘልፈውም? 28እርሱ፦ ምርኮው የረዘመ ነውና ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አታክልትም ተክላችሁ ፍሬዋን ብሉ ብሎ ወደ እኛ ወደ ባቢሎን ልኮአልና።” 29ካህኑም ሶፎንያስ ይህን ደብዳቤ በነቢዩ በኤርምያስ ጆሮ አነበበው።
30የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 31“እግዚአብሔር ስለ አሔልማዊው ስለ ሸማያ እንዲህ ይላል ብለህ ወደ ምርኮኞች ሁሉ ላክ፦ እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችኋልና፥ በሐሰትም እንድትታመኑ አድርጓችኋልና። 32ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሔልማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ እኔም ለሕዝቤ የማደርገውን መልካሙን ነገር የሚያይ ሰው በመካከላችሁ አይኖርላቸውም፤ ይላል እግዚአብሔር፤ በእግዚአብሔር ላይ ዐመፃን ተናግሮአልና።”#ምዕ. 29 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 36 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 29: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in