ወደ ዕብራውያን 6
6
ስለ ንስሓ
1ስለዚህም የክርስቶስን የነገሩን መጀመሪያ ትተን ወደ ፍጻሜው እንሂድ፤ እንግዲህ ደግሞ ሌላ መሠረት እንዳትሹ ዕወቁ፤ ይኸውም ከሞት ሥራ ለመመለስ፥ በእግዚአብሔርም ለማመን፥ 2ጥምቀትን፥ በአንብሮተ እድ መሾምን፥ የሙታንን ትንሣኤና የዘለዓለም ፍርድን ለመማር ነው። 3እግዚአብሔርም ቢፈቅድ ይህን ባደረግን ነበር። 4ነገር ግን አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን፥#ግእዙ “ጥምቀትን የተቀበሉትን” ይላል። ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን፥ ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን፥ 5መልካሙን የእግዚአብሔርን ቃል፥ የሚመጣውንም የዓለምን ኀይል የቀመሱትን፥ 6በኋላም የካዱትን እንደ ገና ለንስሓ እነርሱን ማደስ አይቻልም፤ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና፥ ያዋርዱትማልና። 7ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናም ከጠጣች፥ ያንጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መላካም ቡቃያ ታበቅላለች፤ ከእግዚአብሔር ዘንድም በረከትን ታገኛለች። 8#ዘፍ. 3፥17-18። እሾህንና ኵርንችትን ብታወጣ ግን የተጣለች ናት፤ ለመርገምም የቀረበች ናት፤ ፍጻሜዋም ለመቃጠል ይሆናል።
9የተመረጣችሁ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምንም እንኳን እንዲህ ብንላችሁ ሕይወት ወዳለባት ትምህርት እንድትቀርቡ እንታመንባችኋለን። 10እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስለ አገለገላችሁ፥ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችትሁን ሥራ፥ በስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዐመፀኛ አይደለምና። 11ነገር ግን ሁላችሁም በዚች ተስፋችሁ እንዲሁ ትጋታችሁን እስከ መጨረሻው ታሳዩ ዘንድ እንወዳለን። 12ዳተኞች እንዳትሆኑ በሃይማኖትና በትዕግሥት ተስፋቸውን የወረሱትን ሰዎች ምሰሉአቸው።
ስለ ተስፋና ስለ መሐላ
13እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋዉን በሰጠው ጊዜ ይምልበት ዘንድ ከእርሱ የሚበልጥ ሌላ ባይኖር፥ በራሱ ማለ። 14#ዘፍ. 22፥16-17። እንዲህ ብሎ፦“ መባረክን እባርክሃለሁ፥ ማብዛትንም አበዛሃለሁ።” 15ከዚህም በኋላ ታግሦ ተስፋዉን አገኘ። 16ሰው ግን ከእርሱ በሚበልጠው ይምላል፤ የክርክርም መነሻው በመሐላ ይፈጸማል። 17ስለዚህም እግዚአብሔር ተስፋውን ለሚወርሱ ሰዎች ምክሩን እንደማይለውጥ ሊገልጥ ወደደ፤ እንደማይለውጥም በመሓላ አጸናው። 18የእግዚአብሔር ቃል ሐሰት ሊሆን አይቻልም፤ በእርሱ ለተማፀን ተጠብቆልን ባለ ተስፋችንም ማመንን ላጸናን ለእኛ ታላቅ ደስታ አለን።#በግሪኩና በአንዳንድ ግእዝ “እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻለው በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት አለን” ይላል። 19#ዘሌ. 16፥2። ይህችም ተስፋ ነፍሳችን እንዳትነዋወጥ እንደ መልሕቅ የምታጸና ናት፤ 20እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘለዓለም ሊቀ ካህናት ሆኖ ሐዋርያችን ኢየሱስ ከእኛ በፊት ወደ ገባባት መጋረጃም ውስጥ የምታስገባ ናት።
Currently Selected:
ወደ ዕብራውያን 6: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in