YouVersion Logo
Search Icon

ትን​ቢተ ዕን​ባ​ቆም 1

1
1ነቢዩ ዕንባቆም ያየው ሸክም ይህ ነው። 2አቤቱ፥ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፥ አንተም አታድንም። 3በደልንስ ስለ ምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ ነው፣ ጠብና ክርክር ይነሣሉ። 4ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፥ ፍርድም ድል ነሥቶ አይወጣም፣ ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና፣ ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል።
5እናንተ የምትንቁ ሆይ፥ አንድ ቢተርክላችሁ ስንኳ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁና እዩ፥ ተመልከቱ፥ ተደነቁ። 6እነሆ፥ የእነርሱ ያልሆነውን መኖሪያ ይወርሱ ዘንድ በምድር ስፋት ላይ የሚሄዱትን መራሮችንና ፈጣኖችን ሕዝብ ከለዳውያንን አስነሣለሁ። 7እነርሱ የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፣ ፍርዳቸውና ክብራቸው ከራሳቸው ይወጣል። 8ፈረሶቻቸውም ከነብር ይልቅ ፈጣኖች ናቸው፥ ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው፣ ፈረሰኞቻቸውም ይንሳፈፋሉ፥ ከሩቅም ይመጣሉ፥ ለመብልም እንደሚቸኵል ንስር ይበርራሉ። 9ሁሉም ለግፍ ሥራ ይመጣሉ፥ ፊታቸውንም እንደ ምሥራቅ ነፋስ ያቀናሉ፣ ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባሉ። 10በነገሥታት ላይ ያላግጣሉ፥ መሳፍንትም ዋዛ ሆነውላቸዋል፣ በምሽጉ ሁሉ ይስቃሉ፥ አፈሩንም ከምረው ይወስዱታል። 11የዚያን ጊዜም እንደ ነፋስ አልፎ ይሄዳል፥ ይበድልማል፣ ኃይሉንም አምላክ ያደርገዋል።
12አቤቱ፥ የተቀደስህ አምላኬ ሆይ፥ አንተ ከዘላለም ጀምሮ አልነበርህምን? እኛ አንሞትም፣ አቤቱ፥ ለፍርድ ሠርተኸዋል፥ ለተግሣጽም አድርገኸዋል። 13ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፥ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንድ አትችልም፣ አታላዮችንስ ለምን ትመለከታለህ? ኃጢአተኛውስ ከእርሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠው ስለምን ዝም ትላለህ? 14ሰዎችንም እንደ ባሕር ዓሣዎች፥ አለቃም እንደሌላቸው ተንቀሳቃሾች ለምን ታደርጋቸዋለህ? 15ሁሉን በመቃጥን ያወጣል፥ በመረቡም ይይዛቸዋል፥ በአሽክላውም ውስጥ ያከማቻቸዋል፣ ስለዚህ ደስ እያለው እልል ይላል። 16እድል ፈንታው በእነርሱ ሰብታለችና፥ መብሉም በዝቶአልና ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፥ ለአሽክላውም ያጥናል። 17ስለዚህ መረቡን ይጥላልን? አሕዛብንም ዘወትር ይገድል ዘንድ አይራራምን?

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for ትን​ቢተ ዕን​ባ​ቆም 1