መጽሐፈ መክብብ 9
9
1ይህን ሁሉ በአንድነት ለልቤ ሰጠሁ፥ ጻድቃንና ጠቢባን ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ ልቤ ተመለከተች፤ ፍቅር ወይም ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም፥ ሁሉ ወደ ፊታቸው ነው። 2በሁሉም ከንቱነት አለ፥ የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የመልካሙና እንዲሁ የኀጢአተኛው፥ የመሐላኛውና እንዲሁ መሐላን የሚፈራው ድርሻ አንድ ነው። 3ከፀሓይ በታች የተደረገው ክፉ ሁሉ ለሁሉ ነው፤ የሁሉ ድርሻ አንድ ነውና። ደግሞም የሰው ልጆች ልብ ክፋትን ትሞላለች፥ በሕይወታቸው ሳሉ ሁከት በልባቸው አለ፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። 4ከሕያዋን ጋር አንድነት ያለው ማንም ሰው ተስፋ አለውና ከሞተ አንበሳ ያልሞተ ውሻ ይሻላል። 5ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚህ በኋላ ዋጋ የላቸውም። 6ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንአታቸውም በአንድነት እነሆ፥ ጠፍቶአል፤ ከፀሓይ በታችም በሚሠራው ነገር ሁሉ ለዘለዓለም ዕድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።
7እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና፦ ና እንጀራህን በደስታ ብላ፥ በበጎ ልቡናም የወይን ጠጅህን ጠጣ። 8ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። 9በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሓይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ ዕድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሓይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። 10አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና ዐሳብ፥ ዕውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምትችለውን ሁሉ እንደ ኀይልህ አድርግ።
11እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሓይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ጦርነትም ለኀያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለዐዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ያገናኛቸዋል። 12ሰውም ጊዜውን አያውቅም፤ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች ፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ።
13ከፀሓይ በታችም ጥበብን አየሁ፥ እርስዋም በእኔ ዘንድ ታላቅ ናት። 14ታናሽ ከተማ ነበረች፥ ጥቂቶች ሰዎችም ነበሩባት፤ ታላቅ ንጉሥም መጣባት፥ ከበባትም፥ ታላቅ ግንብንም ሠራባት። 15ጠቢብ ድሃ ሰውም በውስጥዋ ተገኘባት፥ ያችንም ከተማ በጥበቡ አዳናት፤ ያን ድሃ ሰው ግን ማንም አላሰበውም። 16እኔም፥ “ከኀይል ይልቅ ጥበብ ትበልጣለች፤ የድሃው ጥበብ ግን ተናቀች ቃሉም አልተሰማችም” አልሁ።
17በስንፍና ከሚፈርዱ ፈራጆች ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች። 18ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፤ አንድ ኀጢአተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 9: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in