ትንቢተ አሞጽ 8
8
ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ
1ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነበረ። 2እርሱም፥ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም፥ “የቃርሚያ ፍሬ የሞላበት ዕንቅብ ነው” አልሁት። እግዚአብሔርም አለኝ፥ “ፍጻሜ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መጥቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ደግሞ ይቅር አልላቸውም። 3ያንጊዜም በመቅደሶቻቸው ዋይ ዋይ ይላሉ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በየስፍራው የሚወድቀው ሬሳ ይበዛልና፤ እነርሱም ይጠፋሉና።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ዝምታን አመጣባቸዋለሁ” ይላል።
የእስራኤል ውድቀት
4ችግረኛውን በጥዋት የምታስጨንቁ፥ የሀገሩንም ድሃ የምትቀሙ እናንተ ሆይ! 5“እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መቼ ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥ ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥ 6ድሃውን በብር፥ ችግረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ በእህላችንም ንግድ እንድንጠቀም ሰንበት መቼ ያልፋል? የምትሉ እናንተ ሆይ! ይህን ስሙ።” 7እግዚአብሔር በያዕቆብ ትዕቢት እንዲህ ብሎ ምሎአል፥ “ሥራችሁን ሁሉ ለዘለዓለም ምንም አልረሳም። 8በውኑ ምድሪቱ ስለዚህ ነገር አትናወጥምን? በእርስዋም የሚኖር ሁሉ አያለቅስምን? ጦርነት እንደ ወንዝ ይፈስሳል፤ እንደ ግብፅም ወንዝ ይሞላል፤ ደግሞም ይወርዳል።#“ደግሞም ይወርዳል” የሚለው በግእዝ የለም። 9በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር ይገባል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ብርሃንም በምድር ላይ በቀን ይጨልማል። 10ዓመት በዓላችሁንም ወደ ልቅሶ፥ ዝማሬያችሁንም ወደ ዋይታ እለውጣለሁ፤ ማቅንም በወገብ ሁሉ ላይ፥ ቡሃነትንም በራስ ሁሉ ላይ ላይ አመጣለሁ፤ እንደ ወዳጅ#ዕብ. “አንድያ ልጅ” ይላል። ልቅሶ አደርጋችኋለሁ፤ ከእርሱም ጋር ያሉት እንደ መከራ ቀን ይሆናሉ።
11“እነሆ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። 12ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥#ግእዝ “ወይትሐመግ ማየ ባሕር” ይላል። ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ፤ አያገኙትምም። 13በዚያ ቀን መልከ መልካሞቹ ደናግልና ጐበዛዝቱ በጥም ይዝላሉ። 14ዳን ሆይ፥ ሕያው አምላክህን! ደግሞም፦ ሕያው የቤርሳቤህን አምላክ ብለው በሰማርያ መማፀኛ የሚምሉ፥ እነርሱ ይወድቃሉ፥ ደግሞም አይነሡም።”
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 8: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in