የሐዋርያት ሥራ 9
9
ሳውል እንደ ተጠራ
1ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ። 2ምንአልባት በመንገድ የሚያገኘው ሰው ቢኖር ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች የሥልጣን ደብዳቤ ከሊቀ ካህናቱ ለመነ። 3ሲሄድም ወደ ደማስቆ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጊዜ መብረቅ ድንገት ከሰማይ ብልጭ አለበት። 4በምድር ላይም ወደቀ፤ ወዲያውም፥ “ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ቃል ሰማ። 5ሳውልም፥ “አቤቱ፥ አንተ ማነህ?” አለው፤ እርሱም፥ “አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾለ ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስሃል”#“በሾለው ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስሃል” የሚለው በአንዳንድ የግሪክ ዘርዕ አይገኝም። አለው። 6እርሱም እየፈራና እየተንቀጠቀጠ፥ “አቤቱ፥ ምን እንዳደርግ ትሻለህ?” አለው፤ ጌታም፥ “ተነሣና ወደ ከተማ ግባ፤ በዚያም ልታደርገው የሚገባህን ይነግሩሃል” አለው። 7ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ድምፅ እየሰሙ ማንንም ሳያዩ ተደንቀው ቆሙ። 8ሳውልም ከምድር ተነሣ፤ ነገር ግን ዐይኖቹ ተገልጠው ሳሉ የሚያየው ነገር አልነበረም፤ እየመሩም ወደ ደማስቆ አገቡት። 9በዚያም ሳያይ ሳይበላና ሳይጠጣ ሦስት ቀን ቈየ።
10በደማስቆም ስሙን ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ ተገልጦ፥ “ሐናንያ” ብሎ ጠራው፤ እርሱም፥ “አቤቱ፥ እነሆኝ” አለ። 11ጌታም፥ “ተነሣና ቅን በምትባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳ ቤትም ከጠርሴስ ሀገር የመጣ ሳውል የሚባል ሰው ፈልግ፤ እርሱ አሁን ይጸልያልና” አለው። 12ሳውልም በራእይ ሐናንያ የሚባል ሰው ወደ እርሱ ገብቶ ያይ ዘንድ እጁን ሲጭንበት አየ። 13ሐናንያ ግን መልሶ እንዲህ አለ፥ “አቤቱ፥ ስለዚህ ሰው በኢየሩሳሌም በቅዱሳኖችህ ላይ የሚያደርገውን ክፉ ነገር ሁሉ ከብዙ ሰዎች ሰምቻለሁ። 14ወደዚህም ከካህናቱ አለቃ አስፈቅዶ የመጣ ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ሊያስር ነው።” 15ጌታችንም እንዲህ አለው፥ “ተነሥና ሂድ፤ በአሕዛብና በነገሥታት፥ በእስራኤል ልጆችም ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና። 16እኔም ስለ ስሜ መከራን ይቀበል ዘንድ እንዳለው አሳየዋለሁ።” 17ያንጊዜም ሐናንያ ሄደ፤ ወደ ቤትም ገባ፤ እጁንም ጫነበትና፥ “ወንድሜ ሳውል፥ በመንገድ ስትመጣ የታየህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታይና መንፈስ ቅዱስ ይመላብህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል” አለው። 18ያንጊዜም ፈጥኖ እንደ ቅርፊት ያለ ነገር ከዐይኖቹ ላይ ተገፎ ወደቀ፤ ዐይኖቹም ተገለጡ፤ ወዲያውም አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ። 19እህልም በላ፤ በረታም፤ ጥቂት ቀንም ከደቀ መዛሙርት ጋር በደማስቆ ሰነበተ። 20ወዲያውኑም “የእግዚአብሔር ልጅ ነው” ብሎ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በየምኵራቦቹ ሰበከ፥ አስተማረም። 21የሰሙትም ሁሉ አደነቁ፤ እንዲህም አሉ፥ “በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሁሉ ይጠላቸው የነበረው ይህ አይደለምን? ስለዚህ ወደዚህ የመጣው እያሰረ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሊወስዳቸው አይደለምን?” 22ሳውል ግን እየበረታ ሔደ፤ በደማስቆም ለነበሩት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ እያስረዳ መልስ አሳጣቸው።
23 #
2ቆሮ. 11፥32-33። ከብዙ ቀንም በኋላ አይሁድ ሳውልን ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ። 24ሳውል ግን በእርሱ ላይ ሊያደርጉት የሚሹትን ዐወቀባቸው፤ ሊገድሉትም በቀንና በሌሊት የከተማውን በር ይጠብቁ ነበር። 25ደቀ መዛሙርትም በሌሊት ወሰዱት፤ በቅርጫትም አድርገው በቅጽሩ ድምድማት ላይ አወረዱት።
26ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ሊገናኛቸው ደቀ መዛሙርትን ፈለጋቸው። ሁሉም ፈሩት፤ የጌታችን ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ አላመኑትም ነበርና። 27በርናባስም አግኝቶ ወደ ሐዋርያት ወሰደው፤ ጌታችንም በመንገድ እንደ ተገለጠለትና እንደ አነጋገረው፥ በደማስቆም በኢየሱስ ስም እንደ አስተማረ ነገራቸው። 28በኢየሩሳሌምም አብሮአቸው ይገባና ይወጣ ነበረ፤ በጌታችን በኢየሱስ ስምም በግልጥ ያስተምር ነበር። 29ከግሪክ ሀገር መጥተው የነበሩትንም አይሁድ ይከራከራቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ ሊገድሉት ፈለጉ። 30ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሳርያ አወረዱት፤ ከዚያም ወደ ጠርሴስ ላኩት።
31በይሁዳ፥ በሰማርያና በገሊላ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በሰላም ኖሩ፤ ታነጹም፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ጸንተው ኖሩ፤ ሕዝቡም በመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት በዙ።
ቅዱስ ጴጥሮስ ኤንያን እንደ ፈወሰ
32ከዚህም በኋላ ጴጥሮስ በየቦታዉ ሲዘዋወር በልዳ ወደሚኖሩት ቅዱሳን ዘንድ ደረሰ። 33በዚያም ኤንያ የተሰኘ ሰውን አገኘ፤ እርሱም ታሞ በአልጋ ከተኛ ስምንት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ ሽባ ነበርና። 34ጴጥሮስም፥ “ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስህ፤ ተነሥና አልጋህን አንጥፍ” አለው፤ ያንጊዜም ተነሣ። 35በልዳና በሳሮና የሚኖሩም ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታችን ተመለሱ።
ስለ ጣቢታ
36በኢዮጴ ሀገርም ጣቢታ የምትባል አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ በትርጓሜውም ዶርቃስ ይሉአታል፤ ፌቆ ማለት ነው፤ እርስዋም ብዙ ደጋግ ሥራ ትሠራ ነበር፤ ምጽዋትም ትሰጥ ነበር። 37ያንጊዜም ታማ ሞተችና በድንዋን አጥበው በሰገነት አስተኙአት። 38ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ነበርና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው ወደ እነርሱ መምጣት እንዳይዘገይ ይማልዱት ዘንድ ሁለት ሰዎችን ወደ እርሱ ላኩ። 39ጴጥሮስም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በደረሰም ጊዜ ወደ ሰገነት አወጡት፤ ባልቴቶችም ሁሉ ወደ እርሱ መጥተው በፊቱ ቆሙ፤ ያለቅሱላትም ነበር፤ ዶርቃስም በሕይወት ሳለች የሠራችውን ቀሚሱንና መጐናጸፊያውን አሳዩት። 40ጴጥሮስም ሁሉን ካስወጣ በኋላ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ወደ በድንዋም መለስ ብሎ፥ “ጣቢታ ሆይ፥ ተነሽ” አላት፤ እርስዋም ዐይኖችዋን ገለጠች፤ ያንጊዜም ጴጥሮስን አየችው፤ ቀና ብላም ተቀመጠች። 41እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና ባልቴቶችንም ጠርቶ እርስዋን አድኖ ሰጣቸው። 42በኢዮጴም ያሉ ሁሉ ይህን ሰሙ፤ ብዙዎችም በጌታችን አመኑ። 43ጴጥሮስም በኢዮጴ በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት ብዙ ቀን ተቀመጠ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 9: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in