የሐዋርያት ሥራ 14
14
ጳውሎስና በርናባስ በኢቆንዮን ስለ አስተማሩት ትምህርት
1ኢቆንዮን በምትባል ከተማም እንደ ሁልጊዜው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ ከአይሁድና ከአረማውያንም ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። 2ማመንን እንቢ ያሉት የአይሁድ ወገኖች ግን የአሕዝብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ፤ አስከፉም።#የግእዙ ዘርዕ “ሰውነታቸውንም አስጨነቋት” ይላል። 3በጌታም ፊት ደፍረው እያስተማሩ፥ እርሱም የጸጋውን ቃል ምስክር እያሳየላቸው፥ በእጃቸውም ድንቅ ሥራና ተአምራትን እያደረገላቸው ብዙ ወራት ኖሩ። 4የከተማውም ሕዝብ ሁሉ ተለያዩ፤ እኩሌቶቹ ወደ አይሁድ፥ እኩሌቶቹም ወደ ሐዋርያት ሆኑ። 5አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላትዋቸውና በድንጋይ ሊደበድቧቸው ተነሡ። 6ሐዋርያትም ይህን ዐውቀው ወደ ሊቃኦንያ ከተሞች ወደ ልስጥራንና ወደ ደርቤን፥ ወደየአውራጃውም ሸሹ። 7በዚያም ወንጌልን ሰበኩ።
ቅዱስ ጳውሎስ ሽባውን ስለ መፈወሱ
8በልስጥራንም እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱም ማኅፀን ጀምሮ ሽባ የሆነ፥ ከቶም ሂዶ የማያውቅ አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። 9እርሱም ጳውሎስን ሲያስተምር ሰማው፤ ጳውሎስም ትኩር ብሎ ተመለከተው፤ እምነት እንዳለውና እንደሚድንም ተረዳ። 10ድምፁንም ከፍ አድርጎ፥ “ተነሥና ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም እልሃለሁ” አለው፤ ወዲያውኑም ተነሥቶ ተመላለሰ። 11ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፥ “አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወረዱ” እያሉ በሊቃኦንያ ቋንቋ ጮኹ። 12በርናባስን ድያ አሉት፤ ጳውሎስንም የትምህርቱ መሪ እርሱ ነበርና ሄርሜን ብለው ጠሩት። 13በከተማውም ፊት ለፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባ አክሊሎችን ወደ ደጃፍ አመጣ፤ ከሕዝቡም ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ።
14ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስም በሰሙ ጊዜ፥ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ፈጥነውም እየጮኹ ወደ ሕዝቡ ሄዱ። 15#ዘፀ. 20፥11፤ መዝ. 145፥6። እንዲህም አሉአቸው፥ “እናንተ ሰዎች፥ ይህን ነገር ለምን ታደርጋላችሁ? እኛስ እንደ እናንተ የምንሞት ሰዎች አይደለንምን? ነገር ግን ይህን ከንቱ ነገር ትታችሁ ሰማይና ምድርን፥ ባሕርንም በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ ወንጌልን እናስተምራችኋለን። 16አሕዛብን ሁሉ በቀድሞ ዘመን እንደ ነበሩበት እንደ ጠባያቸው ሊኖሩ ተዋአቸው። 17ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራን እየሠራ ከሰማይ ዝናምን፥ ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” 18ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በግድ አስተዉአቸው። 19አይሁድም ከአንጾኪያና ከኢቆንያ መጡ፤ ልባቸውንም እንዲያጠኑባቸው#“ልባቸውንም እንዲያጠኑባቸው” የሚለው በግሪኩ የለም። አሕዛብን አባበሉአቸው፤ ጳውሎስንም እየጐተቱ ከከተማ ውጭ አውጥተው በድንጋይ ደበደቡት፤ የሞተም መሰላቸው። 20ደቀ መዛሙርቱም ከበቡት፤ ነገር ግን ተነሥቶ አብሮአቸው ወደ ከተማ ገባ፤ በማግሥቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ሄደ።
ወደ አንጾኪያ ስለ መመለሳቸው
21በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰበኩ፤ ብዙ ሰዎችንም ደቀ መዛሙርት አድርገው ወደ ልስጥራን፥ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። 22የደቀ መዛሙርትንም ልቡና አጽናኑ፤ በሃይማኖትም እንዲጸኑ፦“ በብዙ ድካምና መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ ይገባናል” እያሉ መከሩአቸው። 23ለቤተ ክርስቲያንም ቀሳውስትን ሾሙ፤ ጾሙ፤ ጸለዩም፤ ለሚታመኑበት ለእግዚአብሔርም አደራ ሰጡአቸው። 24ከጲስድያም ዐልፈው ጵንፍልያ ደረሱ። 25ጴርጌን በተባለችው ከተማም ቃሉን ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢጣሊያ ወረዱ። 26ከዚያም ስለሚሠሩት ሥራ ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ወደ ተሰጡበት ወደ አንጾኪያ በመርከብ ሄዱ። 27አንጾኪያም በደረሱ ጊዜ ምእመናኑን ሁሉ ሰብስበው እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ሁሉ፥ ለአሕዛብም የሃይማኖትን በር እንደ ከፈተላቸው ነገሩአቸው። 28ከደቀ መዛሙርትም ጋር አያሌ ቀን ተቀመጡ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 14: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in