YouVersion Logo
Search Icon

የጴ​ጥ​ሮስ መል​እ​ክት 2 2

2
ስለ ሐሰተኞች ነቢያትና መምህራን
1ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ፤ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ 2ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል፤ በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። 3ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም፤ ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።
4እግዚአብሔር ኀጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ 5ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኀጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውሃ ካወረደ፥ 6ኀጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው፥ 7-8ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዐመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዐመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ 9-10ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል። ደፋሮችና ኵሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፤ 11ዳሩ ግን መላእክት በኀይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ፥ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። 12እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ 13የዐመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ 14ምንዝር የሞላባቸው ኀጢአትንም የማይተዉ ዐይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። 15ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዐመፃን ደመወዝ ወደደ፤ 16ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ።
17ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውሃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው። 18ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፤ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። 19ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው “አርነት ትወጣላችሁ፤” እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። 20በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። 21ዕውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። 22“ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤” ደግሞ “የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች፤” እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for የጴ​ጥ​ሮስ መል​እ​ክት 2 2