መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 3
3
እግዚአብሔር ለሳሙኤል በራእይ እንደ ተገለጠለት
1ብላቴናው ሳሙኤልም በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር፤ በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር ቃል ክቡር ነበረ፤ ራእይም አይገለጥም ነበር። 2በዚያም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ ዔሊም በስፍራው ተኝቶ ሳለ፥ ዐይኖቹ መፍዘዝ ጀምረው ነበር። ማየትም አይችልም ነበር። 3የእግዚአብሔርም መብራት ገና አልጠፋም ነበር፤ ሳሙኤልም የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት በእግዚአብሔር መቅደስ ተኝቶ ነበር፤ 4እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ “ሳሙኤል! ሳሙኤል” ብሎ ጠራው፤ እርሱም፥ “እነሆኝ” አለ። 5ወደ ዔሊም ሮጠ፥ “እነሆኝ ስለ ጠራኸኝ መጣሁ” አለው። እርሱም፥ “አልጠራሁህም፤ ተመልሰህ ተኛ” አለው። ሄዶም ተኛ። 6እግዚአብሔርም ደግሞ፥ “ሳሙኤል! ሳሙኤል” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም ተነሥቶ ዳግመኛ ወደ ዔሊ ሄደና፥ “እነሆኝ ስለ ጠራኸኝ መጣሁ” አለ። እርሱም፥ “አልጠራሁህም ተመልሰህ ተኛ” አለው። 7ሳሙኤል ግን ከዚህ በፊት ገና እግዚአብሔርን አላወቀም ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር። 8እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና፥ “እነሆኝ ስለ ጠራኸኝ መጣሁ” አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ልጁን እንደ ጠራው አስተዋለ። 9ዔሊም ሳሙኤልን፥ “ልጄ፥ ሄደህ ተኛ፤ ቢጠራህም፦ አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው፥” አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ። 10እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፤ እንደ ቀድሞውም ጠራው። ሳሙኤልም፥ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ። 11እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፥ “እነሆ የሰማውን ሁሉ ሁለቱን ጆሮዎቹን ጭው የሚያደርግ ነገሬን በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ። 12በዚያም ቀን በቤቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ በዔሊ ላይ አጸናለሁ፤ እኔም ጀምሬ እፈጽምበታለሁ። 13ልጆቹ በእግዚአብሔር ላይ ክፉ እንዳደረጉ ዐውቆ አልገሠጻቸውምና ስለ ልጆቹ ኀጢአት ለዘለዓለም ቤቱን እንደምበቀል አስታውቄዋለሁ። 14ስለዚህም የዔሊ ቤት ኀጢአት በዕጣንና በመሥዋዕት ለዘለዓለም እንዳይሰረይለት ለዔሊ ቤት ምያለሁ።”
15ሳሙኤልም እስኪነጋ ተኛ፥ ማልዶም ተነሥቶ የእግዚአብሔርን ቤት ደጅ ከፈተ። ሳሙኤልም ራእዩን ለዔሊ መንገር ፈራ። 16ዔሊም ሳሙኤልን ጠርቶ፥ “ልጄ ሳሙኤል ሆይ፥” አለ፤ እርሱም፥ “እነሆኝ” አለ። 17እርሱም፥ “እግዚአብሔር የነገረህ ነገር ምንድን ነው? ከእኔ አትሸሽግ፤ ከነገረህና ከሰማኸው ነገር ሁሉ የሸሸግኸኝ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግብህ፤ እንዲህም ይጨምርብህ” አለው። 18ሳሙኤልም ነገሩን ሁሉ ነገረው፤ አንዳችም አልሸሸገውም። ዔሊም፥ “እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ” አለ።
19ሳሙኤልም አደገ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ከቃሉም አንዳች በምድር ላይ አይወድቅም ነበር። 20እስራኤልም ሁሉ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ነቢይ ይሆን ዘንድ የታመነ እንደ ሆነ ዐወቀ። 21እግዚአብሔርም ደግሞ በሴሎ ተገለጠ። እግዚአብሔር ለሳሙኤል ይገለጥለት ነበርና።#ቀጣዩ በዕብ. የለም። ሳሙኤልም ከምድር ዳርቻ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ በእስራኤል ሁሉ የእግዚአብሔር ነቢይ እንደ ሆነ ታመነ። ዔሊም እጅግ አረጀ፥ ልጆቹ ግን በክፋት ጸንተው ኖሩ፤ መንገዳቸውም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 3: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in