የጴጥሮስ መልእክት 5
5
የእግዚአብሔርን መንጋ ስለ መጠበቅ
1እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ 2በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ 3ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኀይል አትግዙ፤ 4የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ። 5እንዲሁም ጐበዞች ሆይ! ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ልበሱ፤ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፤ ለትሑታኑ ግን ጸጋን ይሰጣል።
6እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኀይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 7እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 8በመጠን ኑሩ፤ ንቁም፤ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ 9በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። 10በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ፥ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችሁማል፤ ያበረታችሁማል። 11ለእርሱ ክብርና ኀይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።
የመጨረሻ ሰላምታና ቡራኬ
12እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ። 13ከእናንተ ጋር ተመርጣ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን፥ ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 14በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን። አሜን።
Currently Selected:
የጴጥሮስ መልእክት 5: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in