YouVersion Logo
Search Icon

የዮሐንስ ራእይ 3

3
ለሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን የተላከ መልእክት
1“በሰርዴስም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል፦ ሥራህን አውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል። 2በአምላኬ ፊት ሥራህን ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፤ ለሞት የተቃረቡትንም የቀሩትን ነገሮች አጽና። 3#ማቴ. 24፥43፤44፤ ሉቃ. 12፥39፤40፤ ራእ. 16፥15።እንግዲህ ቃሉን እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስታውስ፤ ጠብቀውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በማናቸውም ሰዓት እንደምመጣብህ ከቶ አታውቅም። 4ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር በሰርዴስ አሉ፤ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። 5#ዘፀ. 32፥32፤33፤ መዝ. 68፥29፤ ራእ. 20፥12፤ ማቴ. 10፥32፤ ሉቃ. 12፥8።ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፤ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፤ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። 6መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።”
ለፊላደልፊያ ቤተ ክርስቲያን የተላከ መልእክት
7 # ኢሳ. 22፥22፤ ኢዮብ 12፥14። “በፊላደልፊያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ‘ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፥ የዳዊትም መክፈቻ ያለው፥ ሲከፍትም፥ ማንም የማይዘጋው፤ ሲዘጋም ማንም የማይከፍተው፤ እርሱ እንዲህ ይላል’፦
8“ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንም ሊዘጋውም አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፤ ስሜንም አልካድህምና። 9#ኢሳ. 49፥23፤ 60፥14፤ ኢሳ. 43፥4።እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። 10የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ለመፈተን በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ። 11እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። 12#ራእ. 21፥2፤ ኢሳ. 62፥2፤ 65፥15።ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለትም ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ስም፥ እንዲሁም አዲሱን ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። 13መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።
ለሎዲቅያ ቤተ ክርስቲያን የተላከ መልእክት
14 # ምሳ. 8፥22። “በሎዲቅያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ የእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ#3፥14 መገኛ፥ መሠረት፥ መንሥኤ። የነበረው እንዲህ ይላል፦
15“ሥራህን አውቃለሁ፥ በራድ ወይም ትኩስ አለመሆንህን። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር። 16እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው። 17‘ሀብታም ነኝና ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፤ አንድም ነገር አያስፈልገኝም፤’ የምትል ስለ ሆንክ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዐይነ ስውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥ 18ሀብታም እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ የምትጐናጸፈውን ነጭ ልብስ፥ እንድታይም ዐይኖችህን የምትኳልበትን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ። 19#ምሳ. 3፥12፤ ዕብ. 12፥6።እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ተነሣሣ፤ ንስሓም ግባ። 20እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። 21እኔም ድል እንደ ነሣሁ፥ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ። 22መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in