YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 4

4
የኢየሱስ ክርስቶስ መፈተን
(ማር. 1፥12-13ሉቃ. 4፥1-13)
1 # ዕብ. 2፥18፤ 4፥15። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በዲያብሎስ እንዲፈተን መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። 2አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። 3ፈታኙ መጥቶ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው። 4#ዘዳ. 8፥3።እርሱ ግን “‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መለሰለት። 5ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወስዶ በቤተ በመቅደሱ ጫፍ ላይ አቆመውና
6 # መዝ. 91፥11፤12። “‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል፤
እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል’
ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ራስህን ወደ ታች ወርውር” አለው። 7#ዘዳ. 6፥16።ኢየሱስም “‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል” አለው። 8እንደገና ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፤ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየውና፥ 9“ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። 10#ዘዳ. 6፥13።ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “ሂድ አንተ ሰይጣን ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፎአልና” አለው። 11ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ተወው፤ እነሆ መላእክት መጥተው አገለገሉት።
ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ
(ማር. 1፥14-15ሉቃ. 4፥14-15)
12 # ማቴ. 14፥3፤ ማር. 6፥17፤ ሉቃ. 3፥19፤20። ኢየሱስ ዮሐንስ እንደታሰረ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ። 13#ዮሐ. 2፥12።ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም ክልል ወደ አለችው በባሕር አጠገብ ወደምትገኝ ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ። 14ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤
15“የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥
በዮርዳኖስ ማዶ ያለ፥ የባሕር መንገድ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤
16 # ኢሳ. 9፥1-2። በጨለማ የተቀመጠ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤
በሞት አገርና በሞት ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው።”
17 # ማቴ. 3፥2። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ መስበክ ጀመረ።
ኢየሱስ አራት ዓሣ አጥማጆችን እንደ ጠራ
(ማር. 1፥16-20ሉቃ. 5፥1-11)
18በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ ሳለ፥ ሁለት ወንድማማቾች፥ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ። 19እርሱም “ኑ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። 20ወዲያውኑ መረባቸውን ጥለው ተከተሉት። 21ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን በታንኳ ውስጥ ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር መረባቸውን ሲጠግኑ አየና ጠራቸው። 22እነርሱም ወዲያውኑ ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።
ኢየሱስ ብዙ ሰዎችን እንዳስተማረና እንደ ፈወሰ
(ሉቃ. 6፥17-19)
23 # ማቴ. 9፥35፤ ማር. 1፥39። ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትን ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝቡ መካከል ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዘዋወር ነበር። 24ዝናው በመላዋ ሶርያ ሁሉ ተሰማ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይ ተይዘው የታመሙትን ሁሉ፥ አጋንንት ያደሩባቸውን፥ በጨረቃ የሚነሣባቸውንና#4፥24 የሚጥል በሽታ ያለባቸው። ሽባዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። 25ከገሊላ፥ ከዐሥሩ ከተሞች፥ ከኢየሩሳሌም፤ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in