የማቴዎስ ወንጌል 15
15
ስለ ሽማግሌዎች ልማድ
(ማር. 7፥1-13)
1በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና እንዲህ አሉት፦ 2“ደቀ መዛሙርትህ ለምን የሽማግሌዎችን ልማድ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና” አሉት። 3እርሱም “እናንተስ ስለ ልማዳችሁ ስትሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? ሲል መለሰላቸው። 4#ዘፀ. 20፥12፤ ዘዳ. 5፥16፤ ዘፀ. 21፥17፤ ዘሌ. 20፥9።እግዚአብሔር ‘አባትህንና እናትህን አክብር’ ደግሞም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት’ ብሎ አዞአልና፤ 5እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ ‘አባቱን ወይም እናቱን “ከእኔ የምትጠቀመው ሁሉ መባ ነው የሚል ሁሉ፥ 6አባቱን አያከብርም”’ ስለ ልማዳችሁም ስትሉ የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። 7እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ እንዲህ ብሎ ትንቢት በትክክል ተናገረ፥
8 #
ኢሳ. 29፥13። “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥
ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው፤
9የሰው ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል።”
10ሕዝቡንም ጠርቶ እንዲህ አላቸው “ስሙ አስተውሉም፤ 11ወደ አፍ የሚገባው ሰውን አያረክሰውም፤ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው።” 12በዚያን ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ቀርበው “ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ ታውቃለህን?” አሉት። 13እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። 14#ሉቃ. 6፥39።ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ።” 15ጴጥሮስም መልሶ “ይህንን ምሳሌ ተርጉምልን” አለው። 16እርሱም “እናንተም እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? 17ወደ አፍ የሚገባው ሁሉ ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ እንደሚወጣ አታስተውሉምን? 18#ማቴ. 12፥34።ከአፍ የሚወጣው ግን ከልብ ይወጣል፤ እነዚህ ሰውን ያረክሱታል። 19ከልብ ክፉ ሐሳብ፥ መግደል፥ ማመንዘር፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። 20ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ናቸው፥ ባልታጠበ እጅ መብላት ግን ሰውን አያረክሰውም።”
ስለ አንዲት ከነዓናዊት ሴት እምነት
(ማር. 7፥24-30)
21ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። 22እነሆ አንዲት ከነዓናዊት ሴት ከዚያ አገር መጥታ “የዳዊት ልጅ ጌታ ሆይ ማረኝ፤ ሴት ልጄ በጋኔን ክፉኛ ተይዛለች” እያለች ጮኸች። 23እርሱ ግን አንድ ቃልም አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ከኋላችን እየጮኸች ነውና አሰናብታት” እያሉ ለመኑት። 24እርሱም “የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች ነው እንጂ ለሌላ አይደለም” ሲል መለሰ። 25እርሷ ግን መጥታ እየሰገደች “ጌታ ሆይ! እርዳኝ” አለች። 26እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላት “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለቡችሎች መጣል መልካም አይደለም።” 27እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ! ነገር ግን ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች። 28በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ” ሲል መለሰላት። ሴት ልጇም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች።
ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችን እንደ ፈወሰ
29ኢየሱስ ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፤ ወደ ተራራም ወጥቶ እዚያ ተቀመጠ። 30ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችን፥ ሽባዎችን፥ ዲዳዎችን፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ መጡ፥ በኢየሱስም እግር ሥር አስቀመጡአቸው፤ እርሱም ፈወሳቸው። 31ሕዝቡም ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ሽባዎች ሲፈወሱ፥ አንካሶች ሲራመዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።
ኢየሱስ አራት ሺህ ሰዎችን እንደመገበ
(ማር. 8፥1-10)
32ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ “ለሕዝቡ አዝንላቸዋለሁ፥ ምክንያቱም ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋል የሚበሉት ግን የላቸውም፤ በመንገድ ላይ እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልፈልግም” አላቸው። 33ደቀ መዛሙርቱም “በዚህ በምድረ በዳ ይህን ሁሉ ሕዝብ የሚያጠግብ እንጀራ ከየት እናገኛለን?” አሉት። 34ኢየሱስም “ስንት እንጀራ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች” አሉት። 35ሕዝቡን መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ 36ሰባቱን እንጀራና ዓሣዎቹን ይዞ አመሰገነ፤ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጡ። 37ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ። 38የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች ውጪ አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ። 39ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ወደ ጀልባዋ ገብቶ ወደ መጌዶል አገር መጣ።
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 15: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in