የማቴዎስ ወንጌል 13
13
የዘሪው ምሳሌ
(ማር. 4፥1-9፤ ሉቃ. 8፥4-8)
1በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ 2#ሉቃ. 5፥1-3።ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ፥ በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር። 3ብዙ ነገርም በምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። 4ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። 5አንዳንዱም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ 6ነገር ግን ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። 7አንዳንዱም በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም በቀለና አነቀው። 8አንዳንዱም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። 9የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።”
10ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ለምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። 11እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። 12#ማቴ. 25፥29፤ ማር. 4፥25፤ ሉቃ. 8፥18፤ 19፥26።ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። 13ለዚህ ነው በምሳሌ የምነግራቸው ምክንያቱም እያዩ አያዩም፥ እየሰሙም አይሰሙም ወይም አያስተውሉም።
14 #
ኢሳ. 6፥9፤10። እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል።
መስማትን ትሰማላችሁ ነገር ግን አታስተውሉም፤
ማየትንም ታያላችሁ ነገር ግን አትመለከቱም።
15በዓይናቸው አይተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥
በልባቸውም አስተውለው፥ ተመልሰው እንዳልፈውሳቸው፥
የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፥
ጆሮአቸው ደንቁሮአል፥ ዓይናቸውም ተጨፍኖአል፤
16 #
ሉቃ. 10፥23፤24። የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባኩ ናቸው። 17እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው ነበር ነገር ግን አላዩም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው ነበር ነገር ግን አልሰሙም።”
የዘሪው ምሳሌ ትርጒም
(ማር. 4፥13-20፤ ሉቃ. 8፥11-15)
18እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። 19የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው መጥቶ በልቡ የተዘራውን ይነጥቀዋል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። 20በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው ደግሞ ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ 21በራሱ ሥር የለውም፤ ነገር ግን ለትንሽ ጊዜ ይቆያል፥ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። 22በእሾህ መካከል የተዘራው፥ ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ጭንቀትና የሃብት ማታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። 23በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ስድሳ አንዱም ሠላሳ ይሰጣል።
በስንዴ መካከል ስላለ እንክርዳድ ምሳሌ
24ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ መልካም ዘርን የዘራ ሰውን ትመስላለች። 25ሰዎቹ ተኝተው ሳለ፥ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። 26ስንዴው በቅሎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም ያንጊዜ ታየ። 27የባለቤቱ ባርያዎችም ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! በእርሻህ ላይ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። 28እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ’ አላቸው። ባርያዎቹም ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?” አሉት። 29እርሱ ግን እንዲህ አላቸው እንክርዳዱን ስትሰበስቡ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። 30እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ ተዉአቸው፤ በመከር ጊዜ አጫጆቹን “አስቀድማችሁ እንክርዳዱን በእሳትም ለማቃጠል ሰብስባችሁ በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱት፤ እላቸዋለሁ።”
የሰናፍጭ ዘር ምሳሌ
(ማር. 4፥30-32፤ ሉቃ. 13፥20-21)
31ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም ሲል ነገራቸው “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ 32እርሷ ከዘሮች ሁሉ ያነሰች ናት፤ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።”
33ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማያት አንዲት ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” 34ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ነገራቸው፤ ያለ ምሳሌም ምንም አልነገራቸውም።
35 #
መዝ. 78፥2። ይህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤
“አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ፤”
የእንክርዳዱ ምሳሌ ትርጒም
36በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም ንገረን፤” አሉት። 37እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ 38እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ደግሞ የክፉው ልጆች ናቸው፤ 39የዘራው ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆቹ መላእክት ናቸው። 40እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። 41የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም እንቅፋቶችን ሁሉና ዓመፃን ይሰበስባሉ፤ 42ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 43#ዳን. 12፥3።በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
ስለተሰወረው መዝገብ፥ ዕንቁና መረብ ምሳሌ
44“መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው በእርሻ ውስጥ አግኝቶ መልሶ የሸሸገው የተሰወረ መዝገብ ትመስላለች፤ ከደስታውም ብዛት ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛው።
45“ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ክቡር ዕንቁ የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ 46ዋጋዋ እጅግ ውድ የሆነ አንዲት ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።
47“ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለችና ከሁሉም ዓይነት ዓሣ የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ 48በሞላች ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካሞቹን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አስቀመጡ፤ ክፉውን ግን ጣሉት። 49በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ክፉዎችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል፤ 50ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
ስለ አዲሱና ስለ አሮጌው መዝገብ
51“ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ “አዎን” አሉት። 52እርሱም “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀመዝሙር የሆነ ጸሐፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል፤” አላቸው።
ኢየሱስን በናዝሬት እንደ ተቃወሙት
(ማር. 6፥1-6፤ ሉቃ. 4፥16-30)
53ኢየሱስም እነዚህን ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ። 54ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ በምኵራባቸው ያስተምራቸው ነበር፥ ተገርመውም እንዲህም አሉ “ይህን ጥበብና ኃይል ከየት አገኘው? 55ይህ የጠራቢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብ፥ ዮሴፍ፥ ስምዖንና ይሁዳ አይደሉምን? 56እኅቶቹስ ሁሉ ከእኛ ጋር ያሉ አይደሉምን? ታዲያ ይህን ሁሉ ከየት አገኘው?” 57#ዮሐ. 4፥44።ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በስተቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። 58ባለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።
Currently Selected:
የማቴዎስ ወንጌል 13: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in