YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ኢያሱ 6

6
ኢያሪኮ መያዝዋና መጥፋትዋ
1ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርሷ የሚገባ ከእርሷም የሚወጣ ማንም አልነበረም። 2ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። 3#ዘኍ. 10፥2-9፤ 2ሳሙ. 6፥15-16።እናንተም ከተማይቱን ትዞሩአታላችሁ፥ ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ ከተማይቱን በቀን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ። 4ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ። 5ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ እርሷ አቅንቶ በቀጥታ ይገባል።” 6የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሱ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በጌታ ታቦት ፊት ይሸከሙ።” 7ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦ “ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ተዋጊዎቹም በጌታ ታቦት ፊት ይሂዱ።”
8ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። 9ተዋጊዎቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። 10ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታሰሙ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ ከዚያን በኋላ ግን ትጮኻላችሁ።” 11እንዲሁ የጌታን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው በዚያ አደሩ።
12ከዚያም በኋላ ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የጌታን ታቦት ተሸከሙ። 13ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከጌታ ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። 14በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ።
15በሰባተኛውም ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሡ፥ ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። 16በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ጌታ ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። 17#ኢያ. 2፥4፤ ዘዳ. 20፥17፤ ዕብ. 11፥31።ከተማይቱም በእርሷም ያለው ሁሉ ለጌታ እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱ ረዓብ ከእርሷም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። 18#ኢያ. 7፥12፤25፤ ዘዳ. 13፥18።እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁታላችሁም። 19ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለጌታ የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ ጌታም ግምጃ ቤት ይግባ።” 20#2መቃ. 12፥15፤ ዕብ. 11፥30።ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ በቀጥታ አቅንቶ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ያዝዋት። 21#ዘፍ. 15፥16፤ ዘዳ. 7፥2።በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።
22 # ኢያ. 2፥13-14። ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አመንዝራይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ።” 23ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው።
24 # ኢያ. 8፥2። ከተማይቱንም በእርሷም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ ብቻ በጌታ ግምጃ ቤት አኖሩት። 25ኢያሪኮንም ሊሰልሉ ኢያሱ የላካቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱን ረዓብን፥ የአባትዋንም ቤተሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርሷም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች።
26 # ኢያ. 9፥23፤ 1ነገ. 16፥34። በዚያን ጊዜም ኢያሱ እንዲህ ብሎ ማለ፦ “ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በጌታ ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኩር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ።” 27#ኢያ. 1፥5።ጌታም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ዝናውም በምድር ሁሉ ላይ ተሰማ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in