የዮሐንስ ወንጌል 9
9
ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው እንደ አዳነ
1ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው አየ። 2ደቀ መዛሙርቱም “መምህር ሆይ! ይህ ሰው ዐይነ ስውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአትን የሠራው ማን ነው? እርሱ ነው ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጠየቁት። 3ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። 4ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። 5#ማቴ. 5፥14፤ ዮሐ. 8፥12።በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።” 6ይህንንም ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ፤ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች ቀባና 7“ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ፤” አለው፤ ትርጓሜውም “የተላከ” ማለት ነው። ስለዚህም ሄዶ ታጠበ፤ እያየም መጣ። 8ጐረቤቶቹና ቀድሞ ሲለምን አይተውት የነበሩ “ይህ ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለምን?” አሉ። 9ሌሎችም “እርሱ ነው፤” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ “እርሱን ይመስላል እንጂ፥ እርሱ አይደለም፤” አሉ፤ እርሱ “እኔ ነኝ፤” አለ። 10ታድያ “ዐይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” አሉት። 11እርሱ መልሶ “ኢየሱስ የሚባለው ሰው ጭቃ አድርጎ ዐይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ፤’ አለኝ፤ ሄጄ ታጥቤም አየሁ፤” አለ። 12“ያ ሰው ወዴት ነው?” አሉት። “አላውቅም” አለ።
13በፊት ዐይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዐይኖቹን የከፈተበት ቀን ሰንበት ነበረ። 15ስለዚህ ፈሪሳውያን እንዴት እንዳየ እንደገና ጠየቁት። እርሱም “ጭቃ በዐይኖቼ አኖረ፤ ታጠብሁም፤ አያለሁም፤” አላቸውም። 16ከፈሪሳውያንም አንዳንዶቹ “ይህ ሰው ሰንበትን አያከብርምና ከእግዚአብሔር አይደለም፤” አሉ። ሌሎች ግን “ኃጢአትኛ ሰው እንደነዚህ ያሉ ምልክቶችን ሊያደርግ እንዴት ይችላል?” አሉ። በመካከላቸውም መለያየት ሆነ። 17ከዚህም የተነሣ ዐይነ ሥውሩን፥ “አንተ ዐይኖችህን ስለ ከፈተ፥ ስለ እርሱ ምን ትላለህ?” ደግሞ አሉት። እርሱም “ነቢይ ነው፤” አለ።
18አይሁድ የዚያን ማየት የቻለውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ፥ ዐይን ሥውር እንደ ነበረና ማየትም እንደ ጀመረ አላመኑም፤ 19እነርሱንም “እናንተ ዐይን ሥውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል?” ብለው ጠየቁአቸው። 20ወላጆቹም መልሰው “ይህ ልጃችን እንደሆነ ዐይነ ስውርም ሆኖ እንደ ተወለደ እናውቃለን፤ 21ዳሩ ግን አሁን እንዴት ማየት እንደቻለ አናውቅም፤ ወይም ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ እራሱ መናገር ይችላል፤” አሉ። 22ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህንን አሉ፤ “እርሱ#9፥22 ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤” ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና። 23ስለዚህ ወላጆቹ “ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱን ጠይቁት፤” አሉ።
24ስለዚህ ዐይን ሥውር የነበረውን ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ጠርተው “እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን፤” አሉት። 25እርሱም መልሶ “ኀጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዐይን ሥውር እንደ ነበርሁ፥ አሁንም እንደማይ፥ ይህንን አንድ ነገር አውቃለሁ፤” አለ። 26ደግመውም “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይኖችህን ከፈተ?” አሉት። 27እርሱም መልሶ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አልሰማችሁምም፤ ስለምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትፈልጋላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀመዛሙርቱ ልትሆኑ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። 28ተሳድበውም “አንተ የእርሱ ደቀመዝሙር ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ 29እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤” አሉት። 30ሰውዬው መለሰ፤ እንዲህም አላቸው “ከወዴት እንደሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፤ ዳሩ ግን ዐይኖቼን ከፈተ። 31እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር፥ ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን። 32ዐይን ሥውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዐይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ 33ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ሊያደርግ ባልቻለ ነበር።” 34መልሰው “አንተ ሙሉ በሙሉ በኃጢአት ተወልድህ፤ እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት። ወደ ውጭም አወጡት።
35ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፤ ሲያገኘውም “አንተ በሰው ልጅ#9፥35 “በእግዚአብሔር ልጅ” የሚሉ ብራናዎችም አሉ። ኢየሱስ እራሱን “የሰው ልጅ” እያለ በተደጋጋሚ ይጠራል፤ ዓለም ከመፈጠሩ የነበረን፥ በዓለም መጨረሻም ለመፍረድም የሚመጣን መሢሕ ያመለክታል። ታምናለህን?” አለው። 36እርሱም መልሶ “ጌታ ሆይ! በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” አለ። 37ኢየሱስም “አይተኸዋል፤ ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው፤” አለው። 38እርሱም “ጌታ ሆይ! አምናለሁ፤” አለ፤ ሰገደለትም። 39ኢየሱስም “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ፤” አለ። 40ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያንም መሀል ይህንን ሰምተው “እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” አሉት። 41ኢየሱስም አላቸው “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን ‘እናያለን’ ትላላችሁ፤ ኀጢአታችሁም በዚያው ይኖራል።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 9: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in