ትንቢተ ኤርምያስ 25
25
የባቢሎን ምርኮ አስቀድሞ መነገሩ
1 #
2ነገ. 24፥1፤ 2ዜ.መ. 36፥5-7፤ ዳን. 1፥1፤2። በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በመጀመሪያው ዓመት፥ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2ይህንም ቃል ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉና በኢየሩሳሌም ለተቀመጡ ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረው፦ 3ከይሁዳ ንጉሥ ከአሞጽ ልጅ ከኢዮስያስ ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባሉት በእነዚህ በሀያ ሦስቱ ዓመታት፥ የጌታ ቃል ወደ እኔ መጣ፥ እኔም ማልጄ ተነሥቼ ተናገርኋችሁ፤ ተናገርሁ፥ ሆኖም ግን አልሰማችሁም። 4ጌታም ማልዶ ተነሥቶ ባርያዎቹን ነቢያትን ሁሉ ወደ እናንተ ላከ፤ ልኮም ግን እናንተ አላደመጣችሁም፥ ለመስማትም ጆሮአችሁን አላዘነበላችሁም። 5እርሱም፦ ሁላችሁ እናንተ ከክፉ መንገዳችሁና ከሥራችሁ ክፋት ተመለሱ፤ ጌታም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣችሁ ምድር ተቀመጡ። 6ልታገለግሉአቸውና ልትሰግዱላቸው ሌሎችን አማልክት አትከተሉ፥ ክፉም እንዳላደርግባችሁ በእጃችሁ ሥራ አታስቈጡኝ አለ። 7ለእናንተ ጉዳት እንዲሆን በእጃችሁ ሥራ አስቆጣችሁኝ እንጂ አልሰማችሁኝም፥ ይላል ጌታ። 8ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ቃሎቼን አልሰማችሁምና 9እነሆ፥ የሰሜንን ወገኖች ሁሉ እልካለሁ ይላል ጌታ፥ ባርያዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እወስዳለሁ፥ በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች፥ በዙሪያዋም ባሉ በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ ላይ አመጣቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፥ ለመሣቀቂያና ለማፍዋጫም ለዘለዓለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ። 10#ኤር. 7፥34፤ 16፥9፤ ራእ. 18፥22፤23።ከእነርሱም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የሙሽራውን ድምፅና የሙሽራይቱን ድምፅ፥ የወፍጮንም ድምፅ የመብራትንም ብርሃን አስቀራለሁ። 11#2ዜ.መ. 36፥21፤ ኤር. 29፥10፤ ዳን. 9፥2።ይህችም ምድር ሁሉ ባድማና መሣቀቂያ ትሆናለች፤ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ያገለግላሉ።
12ሰባው ዓመትም በተፈጸመ ጊዜ፥ የባቢሎንን ንጉሥና ያንን ሕዝብ ስለ ኃጢአታቸው እቀጣለሁ፥ ይላል ጌታ፥ የከለዳውያንንም ምድር ለዘለዓለም ባድማ አደርጋታለሁ። 13በእርሷም ላይ የተናገርሁትን ቃሎቼን ሁሉ፥ ማለት ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ትንቢት የተናገረውን በዚህች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር አመጣለሁ። 14ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት ደግሞ እነርሱን ይገዙአቸዋል፤ እኔም እንደ አድራጎታቸውና እንደ እጃቸው ሥራ እከፍላቸዋለሁ።
የጌታ የቁጣው ጽዋ
15የእስራኤል አምላክ ጌታ እንዲህ አለኝ፦ “የዚህን ቁጣ የወይን ጠጅ ጽዋ ከእጄ ውሰድ አንተንም የምልክባቸውን አሕዛብን ሁሉ አጠጣቸው። 16በመካከላቸውም ከምልከው ሰይፍ የተነሣ ይጠጣሉ ይወላገዳሉም ያብዳሉም።” 17ከጌታም እጅ ጽዋውን ወሰድሁ፥ ጌታም እኔን የላከባቸውን አሕዛብ ሁሉ አጠጣኋቸው። 18ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ባድማና መሣቀቂያ ማፍዋጫም እርግማንም ላደርጋቸው፥ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች ነገሥታትዋንም አለቆችዋንም አጠጣኋቸው። 19የግብጽንም ንጉሥ ፈርዖንን ባርያዎቹንም አለቆቹንም ሕዝቡንም ሁሉ፥ 20የተደባለቀውንም ሕዝብ ሁሉ፥ የዑፅ ምድር ነገሥታትንም ሁሉ፥ የፍልስጥኤም ምድር ነገሥታትንም ሁሉ አስቀሎናንም ጋዛንም አቃሮንንም የአዛጦንንም ትሩፍ፥ 21ኤዶምያስንም፥ ሞአብንም፥ የአሞንም ልጆች፥ 22የጤሮስን ነገሥታትም ሁሉ፥ የሲዶናን ነገሥታትም ሁሉ፥ በባሕር ማዶ ያለች የደሴት ነገሥታትንም፥ 23ድዳንንም፥ ቴማንንም፥ ቡዝንም፥ የጠጉራቸውንም ማዕዘን የሚቈርጡትን ሁሉ፥ 24የዓረብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድረ በዳ የሚቀመጡ የድብልቅ ሕዝብ ነገሥታትንም ሁሉ፥ 25የዘምሪ ነገሥታትንም ሁሉ፥ የኤላም ነገሥታትንም ሁሉ፥ የሜዶን ነገሥታትንም ሁሉ፥ 26አንዱን ከሌላው በመቀጠል፥ ቅርብና ሩቅ የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ፥ በምድር ፊት ላይ ያሉ የዓለም መንግሥታትንም ሁሉ አጠጣኋቸው፤ የሼሻክም ንጉሥ ከእነርሱ በኋላ ይጠጣል።
27አንተም፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በመካከላችሁ ከምልከው ሰይፍ የተነሣ ጠጡ፥ ስከሩም፥ አስታውኩም፥ ውደቁም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሡም በላቸው። 28ጽዋውንም ከእጅህ ተቀብለው ለመጠጣት እንቢ ቢሉ፦ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ፈጽማችሁ ትጠጣላችሁ። 29እነሆ፥ ስሜ የተጠራባት ከተማ ላይ ክፉን ነገር ማምጣት እጀምራለሁ፤ በውኑ እናንተ ፈጽሞ ያልተቀጣችሁ ትሆናላችሁን? በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ያለ ቅጣት አትቀሩም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ በላቸው።
30ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ቃላት በእነርሱ ላይ ትንቢት ትናገራለህ፥ እንዲህም ትላቸዋለህ፦ ጌታ በላይ ሆኖ ይጮኻል፥ በቅዱስ ማደሪያውም ሆኖ ድምፁን ያሰማል፤ በበረቱ ላይ እጅግ ይጮኻል፥ ወይንም እንደሚጠምቁ በምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይጮኻል። 31ጌታ ከአሕዛብ ጋር ሙግት አለውና ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይደርሳል፤ ከሥጋ ለባሽ ሁሉ ጋር ይፋረዳል፥ ኃጢአተኞችንም ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል፥ ይላል ጌታ።
32የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር ከሕዝብ ወደ ሕዝብ ይወጣል፥ ጽኑም ዐውሎ ነፍስ ከምድር ዳርቻዎች ይነሣል። 33በዚያም ቀን ጌታ የገደላቸው ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይሆናሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ በምድር ላይ እንደ ጉድፍ ይሆናሉ እንጂ አይሰበሰቡም አይቀበሩምም። 34“ልትታረዱና ልትበተኑ ቀናችሁ ደርሶአልና፥ እንደ ተወደደም የሸክላ ዕቃ ትወድቃላችሁና እናንተ እረኞች፥ አልቅሱ ጩኹም፤ እናንተ የመንጋ አውራዎች፥ በአመድ ውስጥ ተንከባለሉ። 35ከእረኞችም የመሸሻ ስፍራ ከመንጋ አውራዎችም ማምለጫ ይጠፋል። 36ጌታ ማሰማርያቸውን አጥፍቶአልና የእረኞች ጩኸት ድምፅ የመንጋ አውራዎችም ልቅሶ ሆኖአል። 37ከጌታ ጽኑ ቁጣ የተነሣ የሰላም በረት ፈርሶአል። 38እንደ ደቦል አንበሳ መደቡን ለቅቆአል፤ ከአስጨናቂውም ሰይፍና ከጽኑ ቁጣው የተነሣ ምድራቸው ባድማ ሆናለችና።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 25: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in