ትንቢተ ኤርምያስ 23
23
እስራኤል ከስደት በኋላ መታደሱ
1“የማሰማርያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው!” ይላል ጌታ። 2ስለዚህ የእስራኤል አምላክ ጌታ ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል፦ “እናንተ በጎቼን በትናችኋል አባርራችኋቸዋልም አልጐበኛችኋቸውምም፤ እነሆ፥ ስለ ክፉ ሥራችሁ እጐበኛችኋለሁ፥ ይላል ጌታ። 3የመንጋዬንም ትሩፍ ካባረርኋቸው ምድር ሁሉ ወደ በረታቸው ራሴ ሰብሰቤ እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም ያፈራሉ፥ ይበዛሉም። 4የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፥ ዳግመኛም አይፈሩምና አይደነግጡም፥ ከእነርሱም አንድም አይጐድልም፥ ይላል ጌታ።
የዳዊት ጻድቅ ቁጥቋጥ
5 #
ኤር. 33፥14-16። “እነሆ፥ ለዳዊት ጻድቅ ቁጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፥ እርሱም ንጉሥ ሆኖ ይነግሣል፥ ይከናወንለታልም፥ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል። 6በዘመኑም ይሁዳ ይድናል እስራኤልም በደኅንነት ይቀመጣል፥ እርሱም፦ ‘ጌታ ጽድቃችን ነው’ በሚለው በዚህ ስም የሚጠራ ይሆናል።
7“ስለዚህ፥ እነሆ፦ ‘የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ያወጣ በሕያው ጌታ እምላለሁ!’ ብለው ዳግመኛ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ፤ 8ነገር ግን፦ የእስራኤልን ቤት ዘር ከሰሜን አገርና ካሰደድኋቸውም አገሮች ሁሉ ያወጣና የመራ በሕያው ጌታ እምላለሁ!” ይላሉ፤ ከዚያም በምድራቸው ይቀመጣሉ።
የሐሰተኛ ነብያት ተስፋ መወገዙ
9ስለ ነቢያት፤ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከጌታ የተነሣ፥ ከቅዱስ ቃላቱም የተነሣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ። 10ምድር በአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳውም ማሰማርዎች ደርቀዋል፤ አካሄዳቸውም ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም። 11ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ ሌላው ቀርቶ በቤቴ ውስጥ እንኳ ክፋታቸውን አግኝቻለሁ፥ ይላል ጌታ። 12ስለዚህ መንገዳቸው በጨለማ እንዳለች እንደ ምታዳልጥ ስፍራ ትሆንባቸዋለች፥ እነርሱም ወደ እርሷ ይገፈተራሉ ተፍገምግመውም ይወድቁባታል፤ እኔም በምጐበኛቸው ዓመት ክፉ ነገርን አመጣባቸዋለሁና፥ ይላል ጌታ።
13በሰማርያ ነቢያት መካከል አጸያፊን ነገር አይቻለሁ፤ በበዓል ትንቢት ይናገሩ ነበር፥ ሕዝቤንም እስራኤልን ያስቱ ነበር። 14#ዘፍ. 18፥20፤ ሕዝ. 16፥49።በኢየሩሳሌምም ነቢያት መካከል አስደንጋጭ ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ በሐሰትም ይሄዳሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ የክፉ አድራጊዎችን እጅ ያበረታሉ፤ ሁላቸውም እንደ ሰዶም የሚኖሩባትም እንደ ገሞራ ሆኑብኝ። 15ስለዚህ ስለ ነብያት የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፥ ከኢየሩሳሌም ነቢያት ዘንድ ርኩሰት በምድር ሁሉ ላይ ወጥቶአልና፥ እሬትን አበላቸዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣቸዋለሁ።”
16የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ ትንቢት የሚናገሩላችሁን የነቢያትን ቃላት አትስሙ፤ ከንቱነትን ያስተምሩአችኋል፤ ከጌታ አፍ ሳይሆን ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ ይናገራሉ። 17ለሚንቁኝ ሁልጊዜ፦ ጌታ፦ ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል ይላሉ፤ በልቡም እልከኝነት ለሚሄድ ሁሉ፦ ክፉ ነገር አያገኛችሁም ይላሉ። 18ቃሉን ለማየትና ለመስማት በጌታ ምክር የቆመ ማን ነውና? ቃሉንስ ያደመጠ የሰማስ ማን ነው?
19እነሆ፥ የጌታ ዐውሎ ነፋስ! ቁጣው ወጥቶአል፥ ጥቅል ዐውሎ ነፍስ፤ እርሱም በክፉዎች ራስ ላይ ይወርዳል። 20የጌታ ቁጣ የልቡን አሳብ ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ አይመለስም፤ በኋለኛው ዘመን ፈጽማችሁ ታስተውሉታላችሁ። 21እኔ ሳልልካቸው እነዚህ ነቢያት ሮጡ፤ እኔም ሳልነግራቸው ትንቢትን ተናገሩ። 22በምክሬ ግን ቢቆሙ ኖሮ፥ ለሕዝቤ ቃሎቼን ባሰሙ ነበር፥ ከክፉም መንገዳቸው ከሥራቸውም ክፋት በመለሱአቸው ነበር።
23እኔ የቅርብ አምላክ ነኝን? ይላል ጌታ፥ የሩቅስ አምላክ አይደለሁምን? 24#ጥበ. 1፥7፤ ሲራ. 16፥17።ሰው በስውር ቦታ ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ይላል ጌታ። ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል ጌታ። 25“አለምሁ አለምሁ” እያሉ በስሜ ትንቢትን በሐሰት የሚናገሩትን የነቢያትን ነገር ሰምቻለሁ። 26ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ፥ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ በነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው? 27አባቶቻቸው ስለ በዓል ስሜን እንደ ረሱ፥ እንዲሁ አንዱ ከሌላው ጋር በሚነጋገሩት ሕልሞቻቸው ሕዝቤ ስሜን ለማስረሳት ያስባሉ። 28የሚያልም ነቢይ ሕልምን ይናገር፤ ቃሌም ያለበት ቃሌን በእውነት ይናገር። ገለባ ከስንዴ ጋር ምን አለው? ይላል ጌታ። 29በውኑ ቃሌ እንደ እሳት፥ ድንጋዩንም እንደሚያደቅቅ መዶሻ አይደለችምን? ይላል ጌታ። 30ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንዱ ከሌላው ዘንድ ቃሎቼን በሚሰርቁ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ። 31እነሆ፥ ከምላሳቸው ትንቢትን አውጥተው፦ “እርሱ ይላል” በሚሉ ነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ። 32እነሆ፥ ሐሰትን ትንቢት በሚያልሙ በሚናገሩም፥ በሐሰታቸውና በድፍረታቸውም ሕዝቤን በሚያስቱ በነቢያት ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ፤ እኔም አልላክኋቸውም አላዘዝኋቸውምም፥ ለእነዚህም ሕዝብ በማናቸውም ነገር አይጠቅሙአቸውም፥ ይላል ጌታ።
33“ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፦ ‘የጌታ ሸክም ምንድነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ፦ ‘ሸክሙ እናንተ ናችሁ፥ እጥላችኋለሁም፥ ይላል ጌታ’ ትላቸዋለህ። 34ነቢይና ካህን ሕዝቡም ‘የጌታ ሸክም’ ብሎ ቢናገር፥ ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ። 35እያንዳንዱም ለባልንጀራው፥ እያንዳንዱም ለወንድሙ እንዲህ ይበልስ፦ ‘ጌታ የመለሰው ምንድነው? ጌታስ ምን ነገር ተናገረ?’ 36ለሰው ሁሉ ቃሉ ሸክም ይሆንበታልና ‘የጌታ ሸክም’ ብላችሁ ከእንግዲህ ወዲህ አትጥሩ፤ የሠራዊትን ጌታ የአምላካችንን የሕያው እግዚአብሔርን ቃላት ለውጣችኋልና። 37ለነቢዩ እንዲህ ትለዋለህ፦ ‘ጌታ ምን መለሰልህ?’ ‘ጌታስ የተናገረው ምንድነው?’ 38ነገር ግን፦ ‘የጌታ ሸክም’ ብትሉ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ፦ ‘የጌታ ሸክም’ አትበሉ ብዬ ልኬባችኋለሁና፥ እናንተም ይህን ቃል፦ ‘የጌታ ሸክም’ ብላችኋልና 39ስለዚህ፥ እነሆ፥ ፈጽሜ እረሳችኋለሁ፥ እናንተንም ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ እጥላለሁ። 40የዘለዓለምንም ስድብ፥ ከቶም ተረስቶ የማይጠፋውን የዘለዓለምን እፍረት አመጣባችኋለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 23: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in