ትንቢተ ሆሴዕ 14
14
ነቢዩ ሆሴዕ ንስሐ እንዲገቡ መለመኑ
1ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጉዞቻቸውም ይቀደዳሉ። 2እስራኤል ሆይ! በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ ጌታ ተመለስ። 3ከእናንተ ጋር ቃላትን ውሰዱ፥ ወደ ጌታም ተመለሱ፥ እንዲህም በሉት፦ “በደልን ሁሉ አስወግድ፥ በቸርነትም ተቀበለን፥ በእንቦሳም ፋንታ የከንፈራችንን ፍሬ እንሰጣለን። 4አሦር አያድነንም፤ በፈረስ ላይ አንቀመጥም፤ ድሀ አደጉም በአንተ ዘንድ ምሕረትን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ ለእጆቻችን ሥራ፦ ‘አምላኮቻችን’ ናችሁ አንላቸውም።”
5ቁጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ከዳተኝነታቸውን እፈውሳለሁ፥ በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ። 6ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፤ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሮቹን ይሰድዳል። 7ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል። 8ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፤ እንደ አትክልት ስፍራ ይለመልማሉ፤ እንደ ወይንም ተክል ያብባሉ፤ መዓዛቸውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል። 9ኤፍሬም ሆይ! ከእንግዲህ ወዲህ ከጣዖታት ጋር እኔ ምን አደርጋለሁ? እኔ እመልስለታለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፤ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፤ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል።
10እነዚህን ነገሮች የሚያስተውል ጠቢብ ማን ነው? የሚያውቃቸውስ አስተዋይ ማን ነው? የጌታ መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ ዓመፀኞች ግን ይወድቁበታል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 14: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in