YouVersion Logo
Search Icon

ኦሪት ዘፍጥረት 4

4
ቃየልና አቤል
1አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፥ እሷም ፀነሰች፥ ቃየንንም ወለደች። እርሷም፦ “ወንድ ልጅ በጌታ ርዳታ አገኘሁ” አለች። 2ደግሞም፥ ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፥ ቃየንም መሬትን የሚያርስ ነበረ። 3ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለጌታ መሥዋዕትን አቀረበ፥ 4#ዕብ. 11፥4።እንዲሁም አቤል ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። ጌታም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፥ 5ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተቈጣ፥ ፊቱም ጠቆረ። 6ጌታም ቃየንን አለው፦ “ስለምን ተናደድህ? ፊትህስ ለምን ጠቆረ? 7መልካም ነገር አድርገህ ቢሆን ኖሮ ተቀባይነት አይኖርህም ነበርን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፥ ፍላጎትዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርሷ ልትሰለጥንባት ይገባል።” 8#ጥበ. 10፥3፤ ማቴ. 23፥35፤ ሉቃ. 11፥51፤ 1ዮሐ. 3፥12።ቃየንም ወንድሙን አቤልን፥ “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። በሜዳም ሳሉ፥ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።
9ጌታም ቃየንን፥ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” አለው። እርሱም፥ “አላውቅም፥ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ?” አለ። 10#ዕብ. 12፥24።ጌታም ቃየልን እንዲህ አለው፥ “ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። 11አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። 12ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፥ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” 13ቃየንም ጌታን አለው፦ “ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት። 14እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፥ ከፊትህም እሰወራለሁ፥ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፥ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” 15እግዚአብሔርም ለእርሱ፥ “እንዲህስ አይሆንም! ማንም ቃየንን የሚገድል፥ ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል” አለው። ጌታም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። 16ከዚያም ቃየን ከጌታ ፊት ወጣ፥ ከዔድንም በስተ ምሥራቅ፥ በኖድም ምድር ተቀመጠ።
የቃየል ትውልድ
17ቃየንም ሚስቱን አወቀ፥ ፀነሰችም፥ ሔኖክንም ወለደች፤ ከተማም መሠረተ፤ ከተማይቱንም በልጁም ስም “ሔኖክ” ብሎ ጠራት። 18ሔኖክ ዒራድን ወለደ፤ ዒራድ መሑያኤልን ወለደ፤ መሑያኤል መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤልም ላሜሕን ወለደ፤
19ላሜሕም ሁለት ሚስቶችን አገባ፥ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ጺላ ነበረ። 20ዓዳም ያባልን ወለደች፥ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። 21የወንድሙም ስም ዩባል ነበረ፥ እርሱም በገናንና ዋሽንትን ለሚይዙ አባት ነበረ። 22ጺላም ደግሞ ከናስና ከብረት የሚቀጠቀጥ ዕቃን የሚሠራውን ቱባልቃይንን ወለደች። የቱባልቃይንም እኅት ናዕማ ነበረች። 23ላሜሕም ለሚስቶቹ፥
“ዓዳ እና ጺላ፥ እስቲ አድምጡኝ፥
እናንት የላሜሕ ሚስቶች ሆይ፥ የምለውን ስሙኝ፤
ቢያቆስለኝ ጐልማሳውን ገደልኩ
ብላቴናውንም ስለ መወጋቴ ገደልኩ፤
24“ከሆነ ቃየልን ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት፥
ላሜሕን ግን ሰባ ጊዜ ሰባት።”
ሤትና ሄኖስ
25አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ፥ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም፥ “ቃየን በገደለው በአቤል ምትክ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል” ስትል ሤት አለችው። 26ሴትም ወንድ ልጅ ወለደ። ስሙንም ሄኖስ አለው፤ በዚያን ጊዜም የጌታ ስም በሰው መጠራት ተጀመረ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

YouVersion uses cookies to personalize your experience. By using our website, you accept our use of cookies as described in our Privacy Policy