ኦሪት ዘፍጥረት 10
10
የዓለም በሰው ዘር መሞላት
1የኖኅ ልጆች የሴም፥ የካም፥ እና የያፌት ትውልድ ይህ ነው፥ ከጥፋት ውኃም በኋላ ልጆችን ወለዱ።
2የያፌት ልጆች፦ ጎሜር፥ ማጎግ፥ ማዳይ፥ ያዋን፥ ቱባል፥ ሜሼክ እና ቲራስ ናቸው። 3የጎሜር ልጆች፦ አሽከናዝ፥ ሪፋት እና ቶጋርማ ናቸው። 4የያዋን ልጆች፦ የኤሊሻ፥ የተርሴስ፥ የኪቲምና የሮዳኒም ሰዎች ናቸው። 5ከእነዚህም በባሕር ዳርቻ ሕዝቦች፥ ሁሉም በየምድራቸው፥ በየቋንቋቸው፥ በየነገዳቸው፥ በየሕዝባቸው ተከፋፍለው የሚኖሩ የያፌት ልጆች ዘር ናቸው።
6የካም ልጆች፦ ኩሽ፥ ምጽራይም፥ ፉጥ እና ከነዓን ናቸው። 7የኩሽ ልጆች፦ ሳባ፥ ሐዊላ፥ ሳብታ፥ ራዕማ እና ሳብተካ ናቸው። የራማ ልጆች፥ ሳባ እና ደዳን ናቸው። 8ኩሽም ናምሩድን ወለደ፥ እርሱም በምድር ላይ ቀዳሚው ኃያል ጦረኛ ነበረ። 9በጌታ ፊት ናምሩድ ኃያል አዳኝ ነበረ፥ ስለዚህም፦ “እንደ ናምሩድ በጌታ ፊት ኃያል አዳኝ” ይባላል። 10የእሱም ግዛት መነሻ፥ ሁሉም በሰናዖር አገር የነበሩት፥ ባቢሎን፥ ኤሬክን፥ አካድ፥ እና ካልኔ ናቸው። 11ከዚያም ወደ አሦር ሄደና ነነዌን፥ ረሆቦትን፥ ካላሕን መሠረተ፤ 12እንዲሁም በነነዌና በካላሕ መካከልም ሬሴን መሠረተ፥ እርሷም ታላቂቱ ከተማ ናት። 13የምጽራይም ዘሮች ሉድ፥ ዐናማውያን፥ ለሃባውያን፥ ናፍሐውያን፥ 14ፈትሮሳውያን፥ ከስሉሃውያን (ከእነርሱም ፍልስጥኤማውያን የተገኙባቸው)፥ እና የካፍቶር ሕዝቦች ናቸው።
15የከነዓን ልጆች በኲሩ ጺዶን፥ ተከታዩ ሔት ይባሉ ነበር፤ 16ሌሎቹም የከነዓን ዘሮች ኢያቡሳውያን፥ አሞራውያን፥ ጌርጌሳውያን፥ 17ሒዋውያን፥ ዓርቃውያን፥ ሲናውያን፥ 18አርዋዳውያን፥ ጸማራውያን፥ ሐማታውያን ነበሩ። ከጊዜ በኋላ የከነዓናውያን ጐሣዎች በየስፍራው ተሠራጩ፤ 19በዚህ ዓይነት የከነዓናውያን ድንበር ከሲዶና አንሥቶ፥ በገራር አጠገብ እስካለው እስከ ጋዛ ድረስ፥ ወደ ሰዶም እና ገሞራ፥ አዳማና በላሻዕ አጠገብ እስካለው እስከ ጸቦይም ድረስ ይደርሳል። 20የካም ልጆች በየነገዳቸውና በየቋንቋቸው፥ በየምድራቸውና በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው።
21ለሴምም ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፥ እርሱም የያፌት ታላቅ ወንድምና የዔቦር ልጆች ሁሉ ቅድመ አያት ነው። 22የሴም ልጆች፦ ዔላም፥ አሦር፥ አርፋክስድ፥ ሉድ እና አራም ናቸው። 23የአራም ልጆች፦ ዑፅ፥ ሑል፥ ጌተር እና ሜሼክ ናቸው። 24አርፋክስድ ሼላሕን ወለደ፤ ሼላሕም ዔቦርን ወለደ። 25ዔቦር ሁለት ልጆች ወለደ፤ አንደኛው እርሱ በተወለደበት ዘመን ሕዝቦች ስለ ተከፋፈሉ ፋሌቅ ተባለ፤ ሌላው ዮቅጣን ይባል ነበር። 26የዮቅጣን ልጆች፦ አልሞዳድ፥ ሼሌፍ ሐጻርማዌት፥ ዬራሕ፥ 27ሀዶራም፥ ኡዛል፥ ዲቅላ፥ 28ዖባል፥ አቢማኤል፥ ሳባ፥ 29ኦፊር፥ ሐዊላና ዮባብ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ዘሮች ናቸው። 30እነርሱ የኖሩበት ግዛት በስተ ምሥራቅ ባለው በተራራማው አገር ከሜሻ እስከ ሰፋር ይደርስ ነበር። 31የሴም ልጆች በየነገዳቸውና በየቋንቋቸው፥ በየምድራቸውና በየሕዝባቸው እነዚህ ናቸው።
32ከጥፋት ውሃ በኋላ የምድር ሕዝቦች፥ እነዚህ በየነገዳቸው የተከፋፈሉ የኖኅ ዘሮች ነበሩ፤ ሁሉም የተገኙት ከእነዚህ ከኖኅ ልጆች ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 10: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in