YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ዕዝራ 4

4
ቤተ መቅደሱ እንደገና እንዳይሠራ የተደረገ ተቃውሞ
1የይሁዳና የብንያምም ጠላቶች ምርኮኞቹ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ መቅደስ እየገነቡ እንደሆነ ሰሙ። 2#2ነገ. 17፥24-41።ወደ ዘሩባቤልና ወደ አባቶች አለቆች ቀርበው፦ “እንደ እናንተ አምላካችሁን እንፈልገዋለን፥ የአሦር ንጉሥ ኤሳርሐዶን ወደዚህ ካመጣን ቀን ጀምሮ ለእርሱ እንሠዋ ነበርና፥ ከእናንተ ጋር እንሥራ” አሉአቸው። 3ዘሩባቤል፥ ኢያሱና የቀሩትም የእስራኤል አባቶች አለቆች፦ “የአምላካችንን ቤት ማነፅ ለእኛና ለእናንተ አይደለም፥ እኛ ለብቻችን ሆነን ንጉሥ ቂሮስ የፋርስ ንጉሥ እንዳዘዘን ለጌታ ለእስራኤል አምላክ ቤት እንገነባለን” አሉአቸው። 4የምድሪቱም ሕዝብ የይሁዳን ሕዝብ እጅ ያደክሙ ነበር፥ እንዳይገነቡም ያስፈራሯቸው ነበር፤ 5ከቂሮስ የፋርሱ ንጉሥ ዘመን ሁሉ ጀምሮ እስከ ዳርዮስ የፋርስ ንጉሥ መንግሥት ድረስ ሥራቸውን እንዲያፈርሱ ባለሥልጣኖችን ቀጠሩባቸው።
የኢየሩሳሌም ዳግም መገንባት የገጠመው ተቃውሞ
6 # አስ. 1፥1። በአሐሽኤሩስ መንግሥት፥ በመንግሥቱም መጀመሪያ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሚኖሩት ላይ ክስ ጻፉ።
7በአርጤክስስ ዘመን ቢሽላም፥ ሚትረዳት፥ ጣብኤል ተባባሪዎቹም ወደ ፋርስ ንጉሥ ወደ አርጤክስስ ጻፉ፤ ደብዳቤውም በሶርያ ፊደልና በሶርያ ቋንቋ ተጽፎ ነበር። 8አዛዡ ሬሑምና ጸሐፊው ሺምሻይ ኢየሩሳሌምን የሚመለከት አንድ ደብዳቤ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ ብለው ጻፉ፤ 9አዛዡ ሬሑምና ጸሐፊው ሺምሻይ የቀሩትም ተባባሪዎቻቸው፥ ዳኞቹ፥ ባለሥልጣኖቹ፥ አስተዳዳሪዎቹ፥ ጸሐፍያን፥ የኤርካውያን፥ ባቢሎናውያን፥ ሱሳንካውያን፥ ዴሐውያን፥ ዔላማውያን፥ 10ታላቁና የተከበረው አስናፋር ያፈለሳቸው በሰማርያና በወንዝ ማዶ ያኖራቸው የቀሩትም አሕዛብ ደብዳቤውን ጻፉ።
11አሁንም የላኩት የደብዳቤ ግልባጭ ይህ ነው፦ “ለንጉሡ ለአርጤክስስ፥ አገልጋዮችህ በወንዙ ማዶ ያለ አገር የሚኖሩ ሰዎች፤ አሁንም 12ከአንተ ዘንድ የመጡ አይሁድ ወደ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም እንደመጡ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ዓመፀኛይቱንና ክፉይቱን ከተማ በመስራት፥ ቅጥሮቿንም በማደስ፥ መሠረትዋንም በመጠገን ላይ ናቸው። 13አሁንም ይህች ከተማ ከተገነባች፥ የቅጥሮቿም ሥራ ከተጠናቀቀ፥ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይሰጡ፥ ንጉሡንም እንደሚጎዳ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። 14ስለዚህ አሁን ሁላችን የቤተ መንግሥቱን ጨው እንበላለንና፥ የንጉሡ አለመከበር ማየት አይገባንምና ስለዚህ ልከን ለንጉሡ አስታወቅን፤ 15በአባቶችህ ታሪክ መጽሐፍ ምርመራ ይደረግ በዚያም በታሪክ መጽሐፍ ይህች ከተማ ዓመፀኛ እንደ ሆነች፥ ነገሥታትንና አውራጃዎችንም እንደ ጐዳች፥ ከጥንቱም ሽፍትነት በእርሷ እንደ ተጀመረ ታገኛለህ፥ ታውቃለህም፤ ስለዚህም ይህች ከተማ ፈርሳ ነበር። 16ይህችም ከተማ ከተገነባች፥ የቅጥሮቿም ሥራ ከተጠናቀቀ፥ በወንዝ ማዶ ባለ አገር ክፍል እንደሌለህ ለንጉሡ እናስታውቃለን።”
17ንጉሡ እንዲህ የሚለውን መልስ ላከ፦ “ለአዛዡ ለሬሑምና ለጸሐፊውም ለሺምሻይ፥ በሰማርያና በወንዝ ማዶ ባለ አገር ለተቀመጡ ለቀሩት ተባባሪዎቻቸው ሰላም! አሁንም 18ወደ እኛ የላካችሁት ደብዳቤ በፊቴ በግልፅ ተነበበ። 19እኔም አዝዣለሁ፥ ተመረመረም፥ ይህችም ከተማ ከጥንት ጀምራ በነገሥታት ላይ ዓመፀኛ እንደ ነበረች፥ በእርሷም ዓመፅና ሽፍትነት እንደ ተደረገ ተገኘ። 20በኢየሩሳሌምም እጅግ ኃያላን ነገሥታት ነበሩ፥ በወንዝም ማዶ ያለውን አገር ሁሉ ይገዙ ነበር፤ ግብርንና ቀረጥን መጥንንም ይቀበሉ ነበር። 21አሁንም እነዚህ ሰዎች ሥራውን እንዲተዉ፥ እኔም ትእዛዝ እስከምሰጥ ድረስ ይህች ከተማ እንዳትሠራ ትእዛዝ ስጡ። 22ቸልም እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ ለነገሥታቱ ጉዳትና ጥፋት እየበዛ ስለምን ይሄዳል?”
23የንጉሡም የአርጤክስስ ደብዳቤ ግልባጭ በሬሑምና በጸሐፊው በሺምሻይ በተባባሪዎቻቸውም ፊት በተነበበ ጊዜ ፈጥነው ወደ ኢየሩሳሌም ወደ አይሁድ ሄዱ፤ በግድና በኃይልም አስተዉአቸው። 24#ሐጌ 1፥1፤ ዘካ. 1፥1።በዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ ቀረ፤ እስከ ፋርስም ንጉሥ እስከ ዳርዮስ መንግሥት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ ተቋረጠ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in