YouVersion Logo
Search Icon

ትንቢተ ሕዝቅኤል 5

5
በኢየሩሳሌም ላይ የመጣ ሰይፍ
1አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የተሳለ ሰይፍ ውሰድ፥ እንደ ጢም መላጫ ለራስህ ትወስደዋለህ፥ በራስህና በጢምህም አሳልፈው፥ ሚዛንንም ውሰድ ጠጉሩንም ትከፋፍለዋለህ። 2የመከበብም ወራት ሲፈጸም አንድ ሦስተኛውን በከተማይቱ መካከል በእሳት ታቃጥለዋለህ፥ አንድ ሦስተኛውን ወስደህ ዙሪያውን በሰይፍ ትመታዋለህ፥ አንድ ሦስተኛውን ወደ ነፋስ ትበትነዋለህ፥ እኔም ከኋላቸው ሰይፍ እመዝዛለሁ። 3ከዚህም ጥቂት ውሰድ፥ በመጐናጸፊያህም ቋጥራቸው። 4ከእነዚህም እንደገና ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላቸዋለህ፥ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፥ ከእርሱም እሳት ወደ እስራኤል ቤት ሁሉ ትወጣለች።
5ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አገሮች በዙሪያዋ ሆነው፥ በመንግሥታት መካከል የተከልዃት ኢየሩሳሌም ይህች ናት። 6እርሷም ከሕዝቦች ይልቅ በትእዛዛቴ ላይ፥ በዙሪያዋ ካሉ አገሮችም ሁሉ ይልቅ በሕጌ ላይ በክፋቷ አምፃለች፥ እነርሱ ትእዛዛቴን አንቀበልም ብለዋልና፥ በሕጌም አልኖሩምና። 7ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁካታችሁ በዙሪያችሁ ካሉት አገሮች ይልቅ ሆኗል፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንዳሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና 8ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፥ አገሮችም እያዩ በመካከልሽ ፍርድን አመጣብሻለሁ። 9ስለ ርኩሰትሽ ሁሉ እስከ አሁን ያላደረግኹትን፥ ከዚህ በኋላም እርሱን የሚመስል የማላደርገውን ነገር በአንቺ ላይ አደርግብሻለሁ። 10#ሰቆ.ኤ. 4፥10።ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ፥ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፥ ፍርድንም አደርግብሻለሁ፥ ከአንቺም የተረፉትንም ሁሉ ወደ ሁሉም ነፋሳት እበትናለሁ። 11ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና ይላል ጌታ እግዚአብሔር በእድፍሽ ሁሉና በርኩሰትሽም ሁሉ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ እኔም አሳንስሻለሁ፥ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም። 12ከአንቺም አንድ ሦስተኛው በቸነፈር ይሞታሉ፥ በመካከልሽም በራብ ያልቃሉ፥ አንድ ሦስተኛውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ አንድ ሦስተኛውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ፥ በኋላቸውም ሰይፍ እመዝዛለሁ።
13ንዴቴ ያልፋል፥ ቁጣዬም በእነርሱ ላይ እንዲያርፍ አደርጋለሁ፥ እጽናናለሁም፥ ቁጣዬን በእነርሱ ላይ በፈጸምሁ ጊዜ እኔ ጌታ በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ። 14በዙሪያሽም ባሉ አገሮች መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ባድማና መሰደቢያ አደርግሻለሁ።
15በአንቺ ላይ በንዴትና በቁጣ፥ በመዓትም ዘለፋ ፍርድን ባደረግሁብሽ ጊዜ፥ በዙሪያሽ ላሉ አገሮች መሰደቢያና መተረቻ፥ ማስጠንቀቂያና ድንጋጤ ትሆኛለሽ፥ እኔ ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ። 16የሚገድሉና የሚያጠፉ የራብ ፍላፃ በወረወርሁ ጊዜ፥ እንዳጠፋችሁ እወረውራቸዋለሁ፥ በእናንተ ላይ ረሃብን እጨምርባችኋለሁ፥ የምግባችሁንም በትር እሰብራለሁ። 17#ራእ. 6፥8።ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድባችኋለሁ፥ ልጆችሽን ያሳጡሻል፥ ቸነፈርና ደምም በአንቺ በኩል ያልፋሉ፥ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ። እኔ ጌታ ይህን ተናግሬአለሁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in