YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4

4
የአካል አንድነት
1እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ እንድትመላለሱ እለምናችኋለሁ፤ 2#ቈላ. 3፥12-13።በትሕትናና በየዋህነት ሁሉ፥ በትዕግሥትም እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ 3በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። 4በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ 5አንድ ጌታ፥ አንድ እምነት፥ አንድ ጥምቀት፤ 6ከሁሉ በላይ የሚሆን፥ በሁሉም የሚሠራ፥ በሁሉም የሚኖር፥ አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። 7ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። 8#መዝ. 68፥18።ስለዚህ
“ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ፤
ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ፤”
ይላል። 9ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? 10ይህ የወረደው ሁሉን ለመሙላት ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። 11አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ የሰጠ እርሱ ነው፤ 12ይህም የክርስቶስ አካል ለመገንባት፥ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ነው፤ 13ይህም ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ፍጽምናው እስክንደርስ ድረስ ነው። 14ከእንግዲህ እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል፥ በሰዎችም ማታለል ምክንያት፥ በነፈሰው የትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን፥ ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን፥ ሕፃናት መሆን አይገባንም። 15ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየተናገርን፥ በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ እርሱ ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ 16#ቈላ. 2፥19።ከእርሱም የተነሣ መላው አካል በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፥ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።
ስለ አሮጌው እና ስለ አዲሱ ሕይወት
17እንግዲህ አሕዛብ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ፥ በጌታም እለምናችኋለሁ። 18እነርሱ ባለማወቃቸውና በልባቸው ደንዳንነት ምክንያት፥ ልቡናቸው ጨለመ፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ 19ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ፥ በማይረካ ምኞት ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ለሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ። 20እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ 21በእርግጥ ሰምታችሁታልና፤ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ 22#ቈላ. 3፥9።ስለ ቀድሞ አኗኗሯችሁም፥ በሚያታልል ምኞቱ የጎደፈውንና የተበላሸውን፥ አሮጌ ሰው አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤ 23በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፤ 24#ቈላ. 3፥10፤ ዘፍ. 1፥26፤ ጥበ. 9፥3።ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።
የአዲሱ ሕይወት ሥርዓት
25 # ዘካ. 8፥16። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን የሰውነት አካሎች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። 26#መዝ. 4፥4።ተቆጡ፥ ኃጢአትን ግን አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፤ 27ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት። 28የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖረው በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። 29እንደ አስፈላጊነቱ፥ ለሚሰሙት ጸጋን እንዲሰጥ፥ ለማነጽ የሚጠቅም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። 30ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። 31መራርነትና ንዴት ቁጣም፥ ጩኸትና ስድብን ሁሉ፥ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። 32#ቈላ. 3፥13።እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in