YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ 9

9
የጳውሎስ በክርስቶስ ማመን
(የሐዋ. 22፥6-1626፥12-18)
1ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፤ 2በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። 3ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ 4በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ “ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ድምፅ ሰማ። 5“ጌታ ሆይ! ማን ነህ?” አለው። እርሱም “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ለአንተ ይብስብሃል፤” አለው። 6እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ “ጌታ ሆይ! ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?” አለው። ጌታም “ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል፤” አለው። 7ከእርሱም ጋር በመንገድ የሄዱ ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንን ግን ሳያዩ እንደ ዲዳዎች ቁሙ። 8ሳውልም ከምድር ተነሣ፤ ዐይኖቹም በተከፈቱ ጊዜ ምንም አላየም፤ እጁንም ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አገቡት። 9ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም፤ አልጠጣምም።
10በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀመዝሙር ነበረ፤ ጌታም በራእይ “ሐናንያ ሆይ!” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! እነሆኝ፤” አለ። 11ጌታም “ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ 12እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል፤” አለው። 13ሐናንያም መልሶ “ጌታ ሆይ! በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ 14በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው፤” አለ። 15ጌታም “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ 16ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና” አለው። 17ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፤ እጁንም ጭኖበት “ወንድሜ ሳውል ሆይ! ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፤ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ፤” አለ። 18#ጦቢ. 11፥13-15።ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዐይኑ ወደቀ፤ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ 19መብልም በልቶ በረታ።
ጳውሎስ በደማስቆ እንደሰበከ በደማስቆም ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን ኖረ።
20ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ። 21የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና “ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን?” አሉ። 22ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር።
23 # 2ቆሮ. 11፥32፤33። ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤ 24ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤ 25ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት።
ጳውሎስ በኢየሩሳሌም
26ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀመዝሙር እንደሆነ ስላላመኑ ፈሩት። 27በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባውና ጌታን በመንገድ እንዴት እንዳየውና እንደ ተናገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እንዴት እንደ ነገረተረከላቸው። 28በጌታም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እየተናገረ በኢየሩሳሌም ሲወጣና ሲገባ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ 29ከግሪክ አገርም መጥተው ከነበሩት አይሁድ ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ፈለጉ። 30ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ወሰዱት፤ ወደ ጠርሴስም ሰደዱት።
31በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ፤ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር።
ጴጥሮስ በልዳ ኤንያን እንደ ፈወሰ
32ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወረደ። 33በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው አገኘ፤ እርሱም ሽባ ነበረ። 34ጴጥሮስም “ኤንያ ሆይ! ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣ ለራስህም አንጥፍ፤” አለው። ወዲያውም ተነሣ። 35በልዳና በሰሮናም የሚኖሩ ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ተመለሱ።
ጴጥሮስ በኢዮጴ ጣቢታን እንደ አስነሣ
36በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀመዝሙር ነበረች፤ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርሷም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። 37በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሩአት። 38ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። 39ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት፤ መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ። 40ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፤ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ “ጣቢታ ሆይ! ተነሺ፤” አላት። እርሷም ዐይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። 41እጁንም ለእርሷ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት። 42ይህም በኢዮጴ ሁሉ የታወቀ ሆነ፤ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ። 43በኢዮጴም ስምዖን ከሚሉት ከአንድ ቁርበት ፋቂ ጋር አያሌ ቀን ኖረ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in