YouVersion Logo
Search Icon

የሐዋርያት ሥራ 28

28
ጳውሎስ በመላጥያ ደሴት
1በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ#28፥1 በዛሬ ዘመን “ማልታ” የምትባለው ደሴት። እንደምትባለ አወቅን። 2አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። 3ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። 4አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም፤” አሉ። 5እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት፤ አንዳችም አልጐዳችውም፤ 6እነርሱም “ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ “ይህስ አምላክ ነው፤” ብለው አሳባቸውን ለወጡ።
7በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፤ እርሱም በእንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን። 8የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። 9ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤ 10በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፤ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን።
ጳውሎስ ሮም እንደ ደረሰ
11ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፤ በእርሱም የዲዮስቆሮስ ዓላማ ነበረበት። 12ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤ 13ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን። 14በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን። 15ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና። 16ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት።
ጳውሎስ በሮም እንደሰበከ
17ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው “ወንድሞች ሆይ! እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ። 18እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤ 19#የሐዋ. 25፥11።አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። 20ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።” 21እነርሱም “እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፤ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም፤ ወይም አልተናገረብህም። 22ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን፤” አሉት።
23ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር። 24እኩሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፤ እኩሌቶቹ ግን አላመኑም፤ 25እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ፦ መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን
26 # ኢሳ. 6፥9፤10። ወደዚህ ሕዝብ ሂድና፥ መስማትን ትሰማላችሁና
አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤
27በዐይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ በልባቸውም
እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ
ደንድኖአል፤ ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዐይናቸውንም ጨፍነዋል፤ በላቸው።
28ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ማዳን ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል። 29ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ።
30ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤ 31ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽነትና በልበ ሙሉነት ያስተምር ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in