YouVersion Logo
Search Icon

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 5

5
ሁለተኛው የግብጽ ዘመቻ
1በዚያን ጊዜ አንጥዮኩስ በግብጽ ላይ እንደገና ለመዝመት ይዘጋጅ ጀመር፤ 2አርባ በሚሆኑ ቀኖች ውስጥ በከተማዋ ሁሉ የወርቅ ልብስ ለብሰው በአየር የሚወረወሩ ፈረሰኞች ታዩ፤ 3ለጦር የተሰለፉ ወታደሮች፥ ለጦር በተሰለፉ ፈረሰኞች ከወዲያ ወዲህ የሚወረወሩ የጦር መሳሪያዎችና መውጊያዎች፥ የሚወዛወዙ ጋሻዎች፥ ተከምረው የቆሙ ጦሮች፥ የተመዘዙ ሰይፎች፤ ተወርዋሪ መሳሪያዎች፥ የሚብለጨለጩ የወርቅና የተለያዩ የብረት ልብሶች ታዩ። 4ስለዚህ ይህ የጦር ልምምድ መልካም ውጤት እንዲኖረው ሁሉም ይጸልዩ ነበር።
የኢያሶን ዐመጽ፤ የአንጥዮኩስ ኤጲፋኒዮስ ተቃውሞ
5የአንጥዮኩስ ሞት በሐሰት ስለተወራ ኢያሶን ከሺህ ያላነሱ ሰዎችን ይዞ በድንገት የኢየሩሳሌምን ከተማ ወጋ፤ ግንብዋ ፈርሶ ከተማዋ በተያዘች ጊዜ መነላዎስ ሸሽቶ ወደ ምሽግ ገባ። 6ኢያስን ያለርኀራኄ የገዛ ገሩን ሰዎች አጠፋ፤ የገዛ ዘሮቹን፥ ወንድሞቹን ማሸነፍ ትልቅ ጉዳት መሆኑን አላሰበም፤ ድል የነሳቸው ጠላቶቹን እንጂ ወገኖቹን አልመሰለውም። 7በአንድ በኩል ሥልጣን ለመያዝ አልተቻለውም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በከዳተኛነቱ ዕፍረትን ተከናነበ፤ እንደገናም ወደ ስደቱ ቦታ ወደ አሞን አገር ሄደ። 8የጭካኔ ድርጊቱ ፈጻሜውን አገኘ፤ በዓረብ ንጉሥ በአርስጣስዩስ ታሰረ፤ ከከተማ ወጥቶ ሸሸ። በሁሉም ይታደን ነበር፤ ምክንያቱም ሕግ በማፍረሱ ተጠልቷል። ሀገሩንና ሕዝቡን በማጥፋቱ ተተፍቷል። ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄደ። 9ይህ ሰው ብዙ ሰዎችን ከግዛታቸው ምድር ያባረረ፥ ዘሩን ፍለጋና መጠጊያ አገኛለሁ በሚል ወደ እስፖርታ የተጓዘ፤ ነገር ግን በባዕድ አገር ባክኖ የቀረ ሰው ነው። 10እርሱ የብዙ ሰዎችን ዓፅም ላለመቅበር ወርውሮ ጥሏል፤ አሁን ግን ለእርሱ የሚያለቅስለት የለም፤ የቀብር ሥርዓት አልተፈጸመለትም፤ ከአባቶቹ የመቃብር ቦታም አላገኘም። 11ንጉሡ እነዚህን ነገሮች በሰማ ጊዜ የአይሁድ አገር ሰዎች መሸፈታቸውን አወቀ፤ እንደ ዱር አውሬ በቁጣ ተናዶ ከግብጽ ተነሣና ከተማዋን ማመስ ጀመረ። 12ቀጥሎም ወታደሮቹን፥ የሚያገኙዋቸውን ያለርህራሄ እንዲጨፈጭፉና በየቤታቸው የሚገቡትንም እየያዙ እንዲያርዷቸው አዘዘ። 13ወጣቶችንና ሸማግሌዎችንም ፈጁ፤ ወንዶችን፥ እናቶችን እና ሕፃናትንም አረዱ፥ ወጣት ልጃገረዶችንና የሚጠቡ ሕፃናትን ቀነጠሱ። 14በሦስት ቀን ውስጥ ሰማንያ ሺህ ሰዎች የወረራው ሰለባ ሆኑ፤ አርባ ሺህ በውጊያ ላይ ሞቱ፤ ቀሪዎች ደግሞ በባርነት ተሸጡ።
የቤተ መቅደሱ መበዝበዝ
15ይህም አልበቃ ብሎት እጅግ በጣም በተቀደሰው ቤተ መቅደስ ውስጥ መግባት ደፈረ፤ መሪውም ሕጉንና ሀገሩን የካዳው መነላዎስ ነበር። 16በረከሱ እጆቹ የተቀደሱ ዕቃዎችን፥ ሌሎች ነገሥታት ለቤተ መቅደሱ እድገትና ክብር ይሆናሉ ብለው ያቀረቡዋቸውን መባዎች ወሰደ፤ በርኩስ እጁ ዳሰሳቸው። 17አንጥዮኩስ በትዕቢት ሐሳብ ተወጠረ፤ ለጥቂት ጊዜ ልዑል ጌታ በሕዝቡ ኃጢአት ምክንያት እንደተቆጣና ቅዱስ ቦታ ሲደፈርም ዝም ብሎ እንዳየ አልተገነዘበም። 18እነርሱ እንዲህ በብዙ ኃጢአት ላይ ባይወድቁ ኖሮ እርሱም የቤተ መቅደሱን ግምጃ ቤት ለመመርመር ሴሌውከስ ተልኮ እንደነበረው እንደ ሄልዮድሮስ በገረፈው ነበረ፤ ከእዚህ ከድፍረት ሥራው በተቆጠበም ነበር። 19እግዚአብሔር ግን ቅዱስን ቦታ የመረጠው ስለ ሕዝቡ ነው እንጂ ሕዝቡን የመረጠው ስለ ቅዱስ ቦታ አይደለም። 20ስለዚህ የተቀደሰውም በሕዝቡ ላይ የደረሰው መከራ ከመጋራቱ በኋላ በሰላምም ጊዜ ተገቢውን ክብር ተካፍሏል፤ ሁሉን የሚችል አምላክ በተቆጣ ጊዜ እንደ ተጣለ፥ ልዑል ጌታ በታረቀ ጊዜ በክብር ታድሷል። 21አንጥዮኩስ ከበቤተ መቅደሱ አንድ ሺህ ስምንት መቶ መክሊቶች ከወሰደ በኋላ በፍጥነት ወደ አንጾኪያ ተመለሰ፤ በትዕቢቱና እራሱን ከፍ ከፍ በማድረጉ በየብስ ላይ የሚቀዝፈና በባሕር ላይ የሚራመድ መስሎ ታይቶ ነበር፤ 22ግን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ሹማምንት ትቶ ሄደ፤ ከእርሱም ይብስ የከፋውን የፍርግያ ሰውን ፊሊጾስን በኢየሩሳሌም ላይ ሾመው፤ 23በጋሪዝም ተራራ አንድሮኒቆስን የበላይ አደረገው፤ ከዚህም በላይ በክፋቱ ከሁሉም የባሰውን በሀገሩ ሰዎች ላይ ጨካኝ የሆነውን መነላዎስን ሾሞ እዚያ ተወው።
የማሳርኩ አጵሎንዮስ ያከናወናቸው ተግባራት
24አይሁዶችን በጣም ስለጠላቸው ንጉሡ የማሳርኩን አጵሎንዮስን ከሃያ ሁለት ሺህ ሰው ጋር ሆኖ በዕድሜ ከፍ ያሉትን ሰዎች እንዲገድል፤ ሴቶችንና ልጆችን እንዲሸጥ አዘዘ። 25ስለዚህ አጵሎንዮስ ወደ ኢየሩሳሌም ከደረሰ በኋላ ሰላማዊ መስሎ አይሁዶች ሥራ በማይሠሩበት በተቀደሰው ቀን፥ በሰንበት ወታደሮች መሣሪያ ይዘው በሠልፍ እንዲወጡ አዘዘ። 26እነርሱን ለመመልከት ወጥተው የነበሩትን አይሁዳውያንን ሁሉ አስገደለ፤ ከተማዋንም ከወታደሮቹ ጋር ሆኖ ለጦር መሣሪያ ወረራት፤ ብዙ ሰዎችንም ገደለ (ጨፈጨፈ)። 27ይሁዳ መቃቢስ ግን ከዘጠኝ ሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ በረሃ ገባ፤ እርሱና ጓደኞቹ እንዳይረክሱ በማለት ሣር እየበሉ እንደ አራዊት በበረሃ ይኖሩ ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in