1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 29
29
አኪሽ ዳዊትን ወደ ጺቅላግ መልሶ መላኩ
1 #
1ሳሙ. 4፥1። ፍልስጥኤማውያን ሠራዊታቸውን ሁሉ በአፌቅ ሰበሰቡ፤ እስራኤላውያንም በኢይዝራኤል ሸለቆ ባለው ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ 2የፍልስጥኤማውያን ገዢዎች በመቶና በሺህ ሆነው ሲዘምቱ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ከአኪሽ ጋር ደጀን ሆነው ይከተሉ ነበር። 3#1ሳሙ. 27፥7።የፍልስጥኤም ጦር አዛዦችም እነርሱን ባዩ ጊዜ “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን ይሠራሉ?” ሲሉ ጠየቁ፤ አኪሽም፥ “ይህ የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ የነበረው ዳዊት አይደለምን? ከእኔ ጋር መኖር ከጀመረ እነሆ ዓመት አለፈው፤ እኔን ከተጠጋበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምንም በደል አላገኘሁበትም” አላቸው። 4#1ዜ.መ. 12፥19-20።የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን በአኪሽ ላይ ተቆጥተው እንዲህ አሉ፤ “ይህን ሰው እንዲመለስ አድርግ፤ ወደ ሰጠኸው ቦታ ይመለስ ዘንድ ስደደው፤ በውጊያው ላይ ተመልሶ ጠላት እንዳይሆን ከእኛ ጋር አይወርድም። እዚህ ያሉትን የእኛን ሰዎች ራስ ቆርጦ ካልወሰደ በስተቀር፥ ከጌታው ጋር እንዴት ሊታረቅ ይችላል? 5#1ሳሙ. 18፥6-7፤ 21፥12።በዘፈን እየተቀባበሉ፥ ‘ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ግን ዐሥር ሺህ’ ብለው የዘመሩለት ይኸው ዳዊት አይደለምን?” 6ስለዚህም አኪሽ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “አንተ ለእኔ ታማኝ ስለ መሆንህ በሕያው ጌታ እምላለሁ፤ ወደዚህም ጦርነት ዘምተህ ብትዋጋ ደስ ባለኝ ነበር፤ ወደ እኔ ከመጣህበት ጊዜ ጀምሮ እኔን ማሳዘን የሚችል በደል ሠርተህ አላገኘሁህም፤ ግን ሌሎቹ ገዢዎች የአንተን አብሮ መዝመት አልፈቀዱም። 7እንግዲህ ተመልሰህ በሰላም ሂድ፤ የፍልስጥኤማውያንን ገዢዎች ቅር የሚያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ” 8ዳዊትም ለአኪሽ፥ “ለመሆኑ ምን አደረግሁ? እዚህ ከመጣሁበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ድረስ፥ በአገልጋይህ ላይ ምን አገኘህበት? ታዲያ፥ ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋር የማልዋጋው ስለ ምንድነው?” ብሎ ጠየቀው። 9አኪሽም እንዲህ አለው፤ “በእኔ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር መልአክ መልካም እንደሆንህ ዐውቃለሁ፤ የፍልስጥኤማውያን አዛዦች ግን፥ ‘አብሮን ለጦርነት መውጣት የለበትም’ ብለዋል። 10አሁንም አብረውህ ከመጡት ከጌታህ አገልጋዮች ጋር ማለዳ ተነሡ፤ በጥዋት ፀሐይ እንደ ወጣችም ሂዱ” አለው። 11ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ለመመለስ በማለዳ ተነሡ፤ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል ወጡ።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 29: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in