YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 16

16
የስምዖን ልጅ ዮሐንስ ከንዳብዮስን አሸንፎ አባረረ
1ዮሐንስ ወደ ጌዘር መጣና የከንደብዮስን ሥራ ለአባቱ ለስምዖን ነገረው። 2ስምዖን ሁለቱን ታላላቆቹን ልጆቹን ይሁዳንና ዮሐንስን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔና ወነድሞቼ እንዲሁም የአባቴ ቤት ከልጅነታችን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ ከእስራኤል ጠላቶች ጋር ተዋግተናል፤ ብዙ ጊዜም እስራኤልን ለማዳን ዕድል አግኝተናል። 3አሁን እኔ አርጅቻለሁ፤ እናንተም አሁን በእግዚአብሔር ምሕረት በዕድሜ ከፍ ብላችኋል፤ ስለዚህ የእኔንና የወንድሜን ቦታ ይዛችሁ ሂዱ፤ ስለ ሕዝባችን ተዋጉ፤ የእግዚአብሔር እርዳታ ከእናንተ ጋር ይሁን።” 4ከሀገሩ ሃያ ሺህ የጦር ሰዎች፤ እግረኞችና ፈረሰኞችን መረጠ፤ ከንደብዮስን ለመውጋት ገሠገሠ፤ በዋዲን አዳር ሆነ። 5ከዚህ በኋላ በማለዳ ተነስተው ወደ ሜዳው ሂዱ፤ እነሆ ብዙ እግረኛና ፈረሰኛ ጦር ውጊያ ለመግጠም ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር፤ በመካከላቸው ወንዝ ነበር፤ 6ዮሐንስና የእርሱ ሰዎች በእነርሱ ፊት ተሰልፈው ቦታ ቦታቸውን ያዙ፤ እነርሱ ወንዙን ለመሻገር የማይደፍሩ መሆናቸውን አውቆ ዮሐንስ ቀድሞአቸው ወንዙን ተሻገረ፤ የእርሱ ሰዎች ይህን አይተው እሱን ተከትለው ተሻገሩ። 7ፈረሰኛ ጦሩን በእግረኛ ጦር መካከል በማድረግ ወታደሮቹን ከፋፈለ፤ ምክንያቱም የጠላት ፈረሰኛ ጦር በጣም ብዙ ነበርና ነው። 8መለከት ተነፋ፤ ከንደብዮስ ከነሠራዊቱ ተሸነፈ፤ ብዙዎቹ ቆስለው ወደቁ፤ የቀሩት ወደ መሽጉ ሸሽተው ሄዱ። 9በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ቴድሮን ድረስ ተከታተላቸው። 10የሸሹት ሰዎች በአዛጦስ ገጠር እስካሉት ግንቦች ድረስ ሄዱ፤ ዮሐንስ በእሳት አጋያቸው፤ ከጠላት ወገንም አስር ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ ዮሐንስ በሰላም ወደ ይሁዳ አገር ተመለሰ።
የስምዖን አሳዛኝ አሟሟት በዶክ፤ ዮሐንስ የአባቱን ቦታ መተካቱ
11የአቡቦስ ልጅ ጰጠሎሜዎስ የኢያሪኮ በረሃ ሜዳ አዛዥ ሆኖ ተሹሞ ነበር። ብዙ ብርና ወርቅ ነበረው፤ 12ምክንያቱም እርሱ የሊቀ ካህናቱ አማች ነበረ፤ 13ፍላጐቱም በመቀስቀሱ እራሱን የሀገሮች ሁሉ ገዢ ለማድረግ ፈለገ፤ ስለዚህም ስምዖንንና ልጆቹን ለማጥፋት የተንኮል ሐሳብ አደረበት። 14ስምዖን ሰለሀገሪቱ ከተሞች አስተዳዳር ወዲያ ወዲህ እያለ ይደክም ነበረ፤ ከልጆቹ ከማታትያስና ከይሁዳ ጋር ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ የወረደውም በመቶ ሰባ ሰባት (የካቲት 134) ዓመተ ዓለም የሰባጥ ወር በሆነው በአሠራ አንደኛው ቀን ነው። 15የአቡቦስ ልጅ በተንኮል በአንዲት ትንሽ ምሽግ ውስጥ ተቀበላቸው። ይህቺ ምሽግ እርሱ የሠራት ዶክ የምትባል ምሽግ ናት። ትልቅ ግብዣ አዘጋጀላቸው፤ ግን በምሽጉ ውስጥ ሰዎችን ሸሸገ። 16ስምዖንና ልጆቹ ጠጥተው ሞቅ ባላቸው ጊዜ ጰጠሎሜዎስና የእርሱ ሰዎች ተነሥተው የጦር መሣሪያቸውን እነሡና በግብዣው አዳራሽ ውስጥ ስምዖንን ከበቡት፤ እንዲሁም ሁለቱን ልጆቹንና ከአገልጋዮቹ አንዳንዶቹን ገደሉ። 17በእንዲህ ዓይነት ትልቅ የከዳተኛነት ሥራን ሠራ፤ ደግ ለሠራለት በክፉ መለሰ። 18ጶጠሎሜዎስ ያደረገውን ነገር ለንጉሡ ጻፈለት፤ ከተሞችንና ገጠሮችን የሚያስረክቡትና የሚረዱት ወታደሮች እንዲልክለትም ጠየቀው። 19ዮሐንስን ለማጥፋት ሌሎች ሰዎችን ወደ ጌዘር ላከ፤ ብርና ወርቅ፤ ሌላም ስጦታ እንድሰጣችሁ ወደ እኔ ኑ በማለት ለጦር አዛዣች ደብዳቤ ላከ፤ 20ኢየሩሳሌምንና የቤተ መቅደሱን ተራራ እንዲይዙ ሌሎች ሰዎችን ላከ፤ 21ግን አንድ ሰው ቀድሞ ሄደና በጌዘር ለዮሐንስ የአባቱንና የወንድሞቹን መሞት ነገረው፤ በተጨማሪም፤ “አንተንም ለመግደል ሰው ልኳል” ሲለ ነገረው። 22ይህን በሰማ ጊዜ ዮሐንስ በጣም ደነገጠ፤ ሊገድሉት የመጡት ሰዎች ይዞ ገደላቸው፤ ምክንያቱም እርሱን ለመግደል መምጣታቸውን አውቆ ነበርና። 23የቀሩት የዮሐንስ ስራዎች፥ ውጊያዎቹ፥ የፈጸማቸው መልካም ሥራዎች፥ የሠራቸው ግንቦችና ታላላቅ ሥራዎቹም፤ 24በአባቱ ምትክ ሊቀ ካህናት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የሠራው ሁሉ እነሆ በጊዜው መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኛል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in