YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 1

1
አንደኛ መቃብያን
መግቢያ
ታላቁ እስክንድር እና ተከታዮቹ
1የመቄዶንያዊው የፊሊጶስ ልጅ እስክንድር ኪትማውያን አገር (መቄዶንያ) ወጥቶ የፋርስና የሜዶን ንጉሥ የሆነው ዳርዮስን አሸንፎ በቦታው ለመጀመሪያ ጊዜ የግሪካውያን ንጉሥ ከሆነ በኋላ፤ 2ብዙ ጦርነቶችን አደረገ፤ ብዙ ምሽጐችን ያዘ፤ የሀገሪቱን ነገሥታት ገደለ። 3እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ሄደ፤ የብዙ ሕዝቦችን ምርኮ ወሰደ። ምድር በፊቱ ዝም አለች፤ ልቡ ከፍ ከፍ አለና በትዕቢት ተነፋ። 4እጅግ ብርቱ ጦር ሠራዊት አዘጋጀ፤ ለእርሱ ግብር መክፈል የሚገባቸውን አገሮች ገባሮቹ እንዲሆኑ አደረገ። 5ከዚህ በኋላ ታመመ፤ ሊሞት መሆኑንም ተገነዘበ። 6ታላላቅ የጦር መኰንኖችንና ከልጅነት ጀምሮ ከእርሱ ጋር ጦርነት ያደረጉትን ሰዎች ከመሞቱ በፊት መንግሥቱን አከፋፈላቸው። 7እስክንድር የሞተው ዐሥራ ሁለት ዓመት ከነገሠ በኋላ ነው። 8ታላላቅ የጦር መኰንኖቹ በየግዛታቸው ሥልጣን ያዙ፤ 9እርሱ ከሞተ በኋላ ሁሉም ዘውድ ደፉ፤ ልጆቻቸውም ከእነርሱ በኋላ ለብዙ ዓመታት እንዲሁ አደረጉ፤ በምድር ላይ ብዙ ክፋትን ሠሩ። አንጥዮኩስ ኤጲፋንዮስ፥ እስራኤል በግሪካዊ ሥርዓት ተፅዕኖ ሥር 10ከእነርሱም አንድ ክፉ ዘር ወጣ፤ አንጥዮኩስ አጲፋንዮስ ይባላል፤ የንጉሥ አንጥዮኩስ ልጅ ነው። እርሱ በሮም አስረኛ ሆኖ ከተቀመጠ በኋላ በግሪካውያን መንግሥት ጊዜ በአንድ መቶ ሰባ ሰባተኛ ዓመት ላይ ንጉሥ ሆነ። 11በዚያን ጊዜ ከእስራኤል ውስጥ ሕግ አፈራሾች ወጡና ብዙ ሰዎችን አሳሳቱ፥ “ኑ እንሂድና በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ ጋር እንስማማ፤ ምክንያቱም ብዙ ክፉ ነገሮች የመጣብን ከእነርሱ በመለየታችን ነው” አሉ። 12ይህ ሐሳብ ደስ ብሎአቸው 13ከሕዝቡ መካከል ብዙዎች በፍጥነት ወደ ንጉሡ ሄዱ፤ እርሱም የአረማውያን ሕዝቦች የሚያደርጉትን እንዲያደርጉ ሥልጣን ሰጣቸው። 14ስለዚህ እንደ አረማውያን ሕዝቦች ልማድ በኢየሩሳሌም አንድ የእስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ሠሩ። 15ግዛታቸውን ደበቁ፤ ከአረማውያን ጋር ለመስማማት ቅዱሱን ቃል ኪዳን ካዱ፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ሸጡ። የመጀመሪያው የግብጻውያን ዘመቻና የቤተ መቅደሱ መዘረፍ 16አንጥዮኩስ የመንግሥቱን ሥልጣን በሚገባ ካጠናከረና ካደራጀ በኋላ በራሱ ግዛት ላይና በምሥር (በግብጽ) ላይ ለመንገሥ ተነሣሣ። 17ሠረገላዎች፥ ዝሆኖችና ብዙ የጦር ሠራዊት ይዞ ወደ ግብጽ አገር ገባ፤ 18ከግብጽ ንጉሥ ከጰጠሎሜዎስ ጋር ጦርነት ገጠመ፤ ጰጠሎሜዎስ ተሸነፈና ብዙ ቁስለኞችን ትቶ ሸሸ። 19የግብጻውያን ምሽጐች ተያዙ፤ አንጥዮኩስ የግብጽን ምርካኞች ወሰደ። 20ግብጽን አሸንፎ በመቶ አርባ ሦስት ዓመተ ዓለም ተመለሰና ከባድ የጦር ሠራዊት ይዞ በእስራኤልና በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፥ 21በትዕቢት ወደ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ገብቶ የወርቅ መሠዊያውንና የመብራት መቅረዙን፥ ሌሎቹንም ዕቃዎች ሁሉ፥ 22የሕብስት ማቅረቢያ ጠረጴዛውን የመጠጥ ማቅረቢያ ዕቃዎችን፥ ጽዋዎችን፥ የዕጣን ማጨሻ የወርቅ ዕቃዎችን፥ መጋረጃዎችና ዘውዶችን ወሰደ፤ በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ የነበረውን የወርቅ ጌጥ በሙሉ አንሥቶ ወሰደው። 23እንዲሁም ብሩንና ወርቁን፥ ክቡር ዕቃዎችን ወሰደ፤ ያገኛቸውን የቤተ መቅደሱን የሀብት ሥውር መዝገቦችንም ዘረፈ። 24ሁሉንም ይዞ ወደ ሀገሩ ሄደ። ብዙ የሰው ደም አፈሰሰ፤ በትዕቢት የተሞሉ የስድብ ቃሎች ተናገረ። 25በመላው የእስራኤል ሀገር ታላቅ ኀዘን ተደረገ። 26ሹማምንትና ሽማግሌዎች በኀዘን አለቀሱ፤ ወጣቶችና ልጃገረዶች ተጐሳቆሉ፤ የሴት ቁንጅና ደበዘዘ። 27ሙሽራው ዋይ ዋይ አለ፤ ሙሽሪትም በቤት ውስጥ በኀዘን ተኮራመተች። 28ምድር በነዋሪዎችዋ ምክንያት ተንቀጠቀጠች፤ የያዕቆብ (የእስራኤል ቤት) በሙሉ ኀፍረትን ተከናነበ። የአክራን ግንባታና የሚሳርክ ጣልቃ ገብነት 29ከሁለት ዓመት በኋላ ንጉሡ ወደ ይሁዳ ከተሞች አንድ የግብር ሹም ላከ እርሱም ከባድ ጦር ሠራዊት ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 30ለሰዎቹ በውሸት የሰላም ቃል ተናገራቸውና አመኑት፤ ከዚያ በኋላ በድንገት ወደ ከተማዋ ገባ፤ ትልቅ አደጋ ጣለባት፤ በእስራኤል ውስጥ ብዙ ሰዎች ገደለ። 31ከተማዋን ዘረፈ፤ አቃጠለ፤ ቤቶችንና ቅጥሩን አፈራረሰ። 32ሴቶችንና ሕፃናትን ማርከው ወሰዱ፤ ከብቶችንም ወሰዱ። 33ከእዚህ በኋላ የዳዊትን ከተማ ደግሞ ገነቡ፤ በዙሪያዋም ረጅም መካበቢያና ጠንካራ ምሽጐች አደረጉ። ምሽጋቸውም እዚያው ሆነ። 34ሃይማኖትና ሕግ የሌላቸውን ክፉ ሰዎች ጠባቂዎች አደረጉባትና አጠናከሩዋት። 35የጦር መሣሪያና ስንቅ አከማቹባት፤ የሰበሰቧቸውን የኢየሩሳሌምን ምርኮዎች አስቀመጡባት፤ ትልቅ ማጥመጃም ሆነላቸው። 36ይህ ነገር ለቤተ መቅደሱ ወጥመድ ሆነ፤ ለእስራኤልም ሁልጊዜ መጥፎ ተቃራኒ ሆነበት። 37በመቅደሱ ዙሪያ የንጹሐን ደም አፈሰሱ፤ ቅዱሱን ቦታ አረከሱ። 38በእነርሱ ምክንያት የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሸሽተው ሄዱ፤ ከተማዋ የጸጉረ ልውጦች መኖሪያ ሆነች፤ ለትውልዷ እንግዳ ሆነች፤ የገዛ ልጆችዋ ጥለዋት ሄዱ። 39የተበዘበዘው ቤተ መቅደስዋ ባዶውን ቀረ፤ በዓሎችዋ በኀዘን ተለወጡ፤ ሰንበቶችዋ ማላገጫ ሆኑ፤ ክብርዋም ተናቀ። 40የከበረችውን ያህል ተዋረደች፤ ታላቅነትዋም ለኀዘን ቦታውን ለቀቀ። የአሕዛብ አምልኮ መደራጀት 41ንጉሡ በመላው መንግሥቱ የእርሱ የሆኑ ሕዝቦች ሁሉ አንድ እንዲሆነና ሁሉም የራሱን የተለየ ባህል እንዲተው አወጀ። 42አሕዛቦች ሁሉ የንጉሡን ትእዛዝ እሺ ብለው ተቀበሉ። 43ብዙ እስራኤላውያን ለጣዖቶች መሥዋዕት በማቅረብና ሰንበትን በማርከስ አምልኮውን ተቀበሉ። 44እንዲሁም ንጉሡ በሀገራቸው እንግዳ የሆኑትን ልምዶች እንዲከተሉ በማዘዝ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ከተሞች በመልእክተኞች አድርጐ ደብዳቤዎችን ላከ፤ 45ከቤተ መቅደሱ የሚቃጠሉ መባዎችን፥ መሠዋዕቶችንና መጠጦችን እንዲያስወግዱ፥ ሰንበትንና በዓላትን እንዲያረክሱ አዘዘ፥ 46ቤተ መቅደሱንና የተቀደሱ ነገሮችን እንዲያረክሱ፤ 47ለጣዖቶች የተቀደሱ ቦታዎችን መሠዊያዎችን፥ ቤተ መቅደሶችንም እንደሠሩና አሳማዎችንና ያልተፈቀዱ እንስሶችን እንዲሠዉ፤ 48ልጆቻቸውን እንዳያስገርዙ፤ ሁሉን ዓይነት ርክሰት በመሥራት ነፍሳቸውን እንደያሳድፉ አዘዘ፤ 49ይህን ሁሉ የሚያደርጉትም ሁሉ የሙሴን ሕግ በመርሳትና ትእዛዘቹንም በማፍረስ ነው። 50የንጉሡን ትእዛዝ አልፈምም ያለ ሁሉ ይገደላል። 51በዚህ ዓይነት ነው ንጉሡ በእርሱ ሥር ለሚገኙ ዜጎች ሁሉ በጽሑፍ ትእዛዙን ያስተላለፈው፤ በሕዝቡ ሁሉ ላይ ተቆጣጣሪ አደረገበት፤ በየከተማው መሥዋዕቶች እንዲያቀርቡ ወደ ይሁዳ ከተሞች ትእዛዝ አስተላለፈ። 52ከሕዝቡ ብዙ ሰዎች የሙሴን ሕግ በመተው ከአረማውያን ጋር ተስማሙ፤ በሀገሪቱ ላይ ክፉ ሥራ ሠሩ፤ 53እስራኤላውያን በየመደበቂያ ቦታቸው እንዲሸሸጉ አስገደዱአቸው። 54ቄስለው ወር (ከኀዳር 15 እስከ ታኀሣሥ 15) በዓሥራ አምስተኛው ቀን ንጉሡ በሚቀጥለው መሥዋዕት መሠዊያ ላይ የጥፋት ርኩሰት ሠራ፤ በይሁዳ ከተሞች ዙሪያም መሠዊያዎች ተቋቋሙ። 55በቤቶች መዝጊያዎች አጠገብና በአደባባዮች ዕጣን ያጨሱ ነበር። 56የሙሴን ሕግ መጻሕፍት ሲያገኙዋቸውም ቀዳደው በእሳት ውስጥ ይጨምሩዋቸው ነበር። 57የብሉይ ኪዳን መጽሐፈ ይዞ የተገኘና የሙሴን ሕግ የሚያከብር ሰው በንጉሡ ውሳኔ መሠረት ይገደል ነበር። 58ውሳኔውን ሲያፈርሱ የሚያዙ እስራኤላውያን በየወሩ በጭካኔ ይቀጡ ነበር። 59በየወሩ በ 25ኛው ቀን በቤተ መቅደሱ መሠዊያ ላይ በተሠራው መሠዊያቸው ላይ ይሠዉ ነበር። 60ልጆቻቸውን ያስረገዙ ሴቶች በንጉሡ ውሳኔ መሠረት ይገደሉ ነበር። የተረገዙት ሕፃናትም በእናቶቻቸው አንገት ላይ እንዲሰቀሉ ይደረጉ ነበር። 61ቤተሰቦቻቸውና የግርዘት ሥርዓቱን የፈጸሙ ሁሉ ከሞት አያመልጡም ነበር። 62ይሁን እንጂ በእስራኤል ብዙዎች በእምነታቸው ጠንካሮች ሆነው ተገኝተዋል፤ እርኩስ ነገር ላለመብላትመ ኃይል አግኝተዋል። 63እርኩስ ምግብ ከመብላትና ቅዱሱን ቃል ኪዳን ከማርከስ ይልቅ ሞትን መርጠው ሞተዋል። 64በእስራኤል ላይ የወደቀው ቅጣት አስፈሪ ጥፋት ነበር።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in