YouVersion Logo
Search Icon

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5

5
1ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። 2እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስንጠብቅ የእግዚአብሔርን ልጆች እንደምንወድ በዚህ እናውቃለን። 3#ዮሐ. 14፥15።ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ፥ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም። 4ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው። 5ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?
6በውኃና በደም የመጣው ይህ ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በውኃው ብቻ አይደለም ነገር ግን በውኃና በደም ነው። የሚመሰክረውም መንፈሱ ነው፥ መንፈሱ እውነት ነውና። 7ሦስት ምስክሮች አሉ፤ 8መንፈስ ውኃና ደም፤ ሦስቱም አንድ ናቸው። 9የሰውን ምስክርነት የምንቀበል ከሆነ የእግዚአብሔር ምስክርነት ይበልጣል፤ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረው ምስክርነት ይህ ነውና። 10በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በራሱ ምስክር አለው፤ እግዚአብሔርን የማያምን ግን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክርነት ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል። 11#ዮሐ. 3፥36።ምስክርነቱ ይህ ነው፦ እግዚአብሔር የዘለዓለምን ሕይወት ሰጠን፥ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው። 12ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ግን ሕይወት የለውም።
13በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ፥ የዘለዓለም ሕይወት እንዳላችሁ እንድታውቁ ይህን ጽፌላችኋለሁ። 14በእርሱ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንጠይቅ ይሰማናል። 15የምንጠይቀውን እንደሚሰማን ካወቅን፥ የጠየቅነውን እንደ ተቀበልን እናውቃለን። 16ማንም ወንድሙ ለሞት የማያደርስ ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፥ እግዚአብሔርም ለሞት የማያደርስ ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል። ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ። ስለዚህ ይለምን አልልም። 17ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፥ ለሞት የማያበቃ ኃጢአት አለ።
18ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን እንደማያደርግ እናውቃለን፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የተወለደው ራሱን ይጠብቃል፤ ክፉውም አይነካውም።
19እኛ ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን፥ መላው ዓለምም በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።
20የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ፥ እውነት የሆነውን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እውነት በሆነው በእርሱ እንኖራለን፥ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው። 21ልጆች ሆይ፥ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in