1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 28
28
ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን እንዲሠራ መታዘዙ
1ዳዊትም የእስራኤልን አለቆች ሁሉ፥ የነገዶቹንም አለቆች፥ ንጉሡንም በክፍል የሚያገለግሉትን የሠራዊቱ አለቆች፥ ሻለቆቹንም፥ የመቶ አለቆቹንም፥ በንጉሥና በልጆቹ ሀብትና ግዛት ላይ የተሾሙትን፥ ጃንደረቦችንም፥ ጽኑዓን ኃያላኑንም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 2#2ሳሙ. 7፥1-16፤ 1ዜ.መ. 17፥1-14።ንጉሡም ዳዊት ተነሥቶ በመቆም እንዲህ አለ፦ “ወንድሞቼና ሕዝቤ ሆይ! ስሙኝ፤ ለጌታ ለቃል ኪዳኑ ታቦትና ለአምላካችን እግር ማረፊያ የሚሆን የማረፍያ ቤት ለመሥራት እኔ በልቤ አስቤያለሁ፤ ለግንባታም የሚያስፈልገውን አዘጋጅቻለሁ፤ 3እግዚአብሔር ግን፦ ‘የጦር አርበኛ ነህና፥ ደምም አፍስሰሃልና ለስሜ ቤት አትሠራም’ ብሎኛል። 4ነገር ግን የእስራኤል አምላክ ጌታ በእስራኤል ላይ የዘለዓለም ንጉሥ እንድሆን ከአባቴ ቤት ሁሉ መርጦኛል፤ ይሁዳንም አለቃ እንዲሆን መርጦታል፤ ከይሁዳም ቤት የአባቴን ቤት መርጦአል፤ ከአባቴም ልጆች መካከል በእስራኤል ሁሉ ላይ ሊያነግሠኝና ሊመርጠኝ ወደደ። 5ጌታም ብዙ ልጆች ሰጥቶኛልና ከልጆቼ ሁሉ በጌታ መንግሥት ዙፋን ላይ ተቀምጦ በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ ልጄን ሰሎሞንን መርጦታል። 6እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ልጅ እንዲሆንልኝ መርጬዋለሁና፥ እኔም አባት እሆነዋለሁና ልጅህ ሰሎሞን ቤቴንና አደባባዮቼን ይሠራል። 7ትእዛዜንና ፍርዴንም በማድረግ እንደ ዛሬው ቢጸና መንግሥቱን ለዘለዓለም አጸናዋለሁ።’ 8አሁንም የጌታ ጉባኤ እስራኤል ሁሉ እያዩ፥ አምላካችንም እየሰማ፥ ይህችን መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱ፥ ለልጆቻችሁም ለዘለዓለም እንድታወርስዋት የአምላካችሁን የጌታን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ፥ ፈልጉም።
9“አንተም፥ ልጄ ሰሎሞን ሆይ! እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘለዓለም ይጥልሃል። 10አሁንም፥ እነሆ፥ ጌታ ለመቅደስ የሚሆን ቤትን እንድትሠራ መርጦሃልና በርትተህ በቈራጥነት ፈጽመው።”
11ዳዊትም ለመቅደሱ ወለል፥ ለቤቱም፥ ለቤተ መዛግብቱም፥ ለደርቡና ለውስጡም ጓዳዎች፥ ለስርየቱም መክደኛ መቀመጫ ንድፈ ሐሳቡን ለልጁ ለሰሎሞን ሰጠው። 12ደግሞም ለጌታ ቤት አደባባዮችና በዙሪያው ለሚሆኑ ጓዳዎች፥ ለእግዚአብሔርም ቤት ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት፥ ለንዋየ ቅድሳቱም ለሚሆኑ ቤተ መዛግብት በመንፈሱ ያሰበውን ንድፈ ሐሳብ ሁሉ ሰጠው። 13የካህናቱንና የሌዋውያኑንም ክፍላቸውን በጌታም ቤት ለሚያገልግሉበት ሥራ ሁሉ አስታወቀው። በጌታም ቤት ለሚያገለግሉበት ዕቃ ሁሉ፥ 14ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለወርቁ ዕቃ ወርቁን በሚዛን ሰጠው፤ ለአገልግሎት ሁሉ ለሚሆነውም ለብር ዕቃ ሁሉ ብሩን በሚዛን ሰጠው፤ 15ለወርቁም መቅረዞችና ለቀንዲሎቹም ወርቁን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ ለብሩም መቅረዞች እንደ መቅረዙ ሁሉ ሥራ ብሩን በየመቅረዙና በየቀንዲሉ በሚዛን ሰጠው፤ 16ለተቀደሰው ኅብስት ገበታዎች ወርቁን በሚዛን ለገበታዎቹ ሁሉ፥ ብሩንም ለብሩ ገበታዎች ሰጠው፤ 17ለሜንጦቹና ለድስቶቹ ለመቅጃዎቹም ጥሩውን ወርቅ፥ ለወርቁም ጽዋዎች ወርቁን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን፥ ለብሩም ጽዋዎች ብሩን በየጽዋው ሁሉ በሚዛን ሰጠው፤ 18ለዕጣኑም መሠዊያ ንጹሑን ወርቅ በሚዛን፥ ክንፎቻቸውንም ዘርግተው የጌታን ቃል ኪዳን ታቦት የሸፈኑትን የኪሩቤልን የወርቅ ሠረገላ ንድፈ ሐሳብ ሰጠው። 19ዳዊትም፦ “የሥራውን ሁሉ ንድፈ ሐሳብ እንዳውቅ ይህ ሁሉ በጌታ እጅ ተጽፎ መጣልኝ” አለ።
20ዳዊትም ልጁን ሰሎሞንን እንዲህ አለው፦ “ጠንክር፥ አይዞህ፥ አድርገውም፤ አምላኬ እግዚአብሔር አምላክ ከአንተ ጋር ነውና አትፍራ፥ አትደንግጥም፥ ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የሚሆነው ሥራ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ እርሱ አይተውህም፥ አይጥልህምም። 21እነሆም፥ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ሁሉ የሚሆኑ የካህናትና የሌዋውያን ክፍሎች በዚህ አሉ፤ ለሁሉም ዓይነት አገልግሎትና ሥራ በብልሃትና በነፍሱ ፈቃድ የሚሠራ ሁሉ ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አለቆችና ሕዝቡም ሁሉ ፈጽመው ይታዘዙሃል።”
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 28: መቅካእኤ
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in