ወደ ቲቶ 1
1
1የእግዚአብሔር አገልጋይና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነው፥ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች ለማጠንከርና የሃይማኖትንም እምነት ሙሉ በሙሉ እንዲያውቁ ለማድረግ ከተሾመ ከጳውሎስ የተላከ፦
2ይህም እምነት በዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ላይ የተመሠረተ ነው፤ የማይዋሸው አምላክ ይህን ሕይወት ለመስጠት ከዘመናት በፊት ቃል ገባልን። 3ዘመኑም በደረሰ ጊዜ በአዳኛችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ እኔ እንዳበሥር በተሰጠኝ ዐደራ አማካይነት እግዚአብሔር ቃሉን ገለጠ።
4የጋራችን በሆነው እምነት በእውነት ልጄ ለሆንከው ለቲቶ፥ #2ቆሮ. 8፥23፤ ገላ. 2፥3፤ 2ጢሞ. 4፥10።
ከእግዚአብሔር አብና ከአዳኛችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለአንተ ይሁን።
የቲቶ ሥራ በቀርጤስ
5አንተን በቀርጤስ የተውኩበት ምክንያት ያልተስተካከለውን እንድታስተካክልና ባዘዝኩህም መሠረት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን በየከተማው እንድትሾም ነው። 6የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሆነ፥ ስድ በመሆንና ባለመታዘዝ ምክንያት የማይወቀሱ አማኞች ልጆች ያሉት ሰው መሆን ይገባዋል። 7ኤጲስ ቆጶስ (የቤተ ክርስቲያን መሪ) የእግዚአብሔርን ሥራ በዐደራ የተቀበለ ስለ ሆነ የማይነቀፍ መሆን አለበት፤ እንዲሁም የማይኰራ፥ በቶሎ የማይቈጣ፥ የማይሰክር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ለገንዘብ የማይስገበገብ መሆን አለበት። 8ይልቅስ እንግዳ ተቀባይ፥ መልካም የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ራሱን የሚቈጣጠር፥ ትክክለኛ፥ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ፥ በመጠን የሚኖር ይሁን። 9እውነተኛውን ትምህርት በማስተማር ለመምከርና ለተቃዋሚዎችም መልስ ለመስጠት እንዲችል በተማረው መሠረት በአስተማማኝ ቃል ይጽና። #1ጢሞ. 3፥2-7።
10ብዙ ሰዎች፥ ይልቁንም ከአይሁድ ወገን የሆኑ የግዝረትን ሥርዓት የሚከተሉ፥ የማይታዘዙ፥ በከንቱ የሚለፈልፉና የሚያታልሉ አሉ። 11እነዚህን ሰዎች ዝም ማሰኘት ይገባል፤ እነርሱ በሚያሳፍር ትርፍ ለማግኘት የማይገባውን ነገር እያስተማሩ ቤተሰቦችን በሙሉ ያናውጣሉ። 12ከእነርሱ አንዱ የሆነው የገዛ ራሳቸው ነቢይ “የቀርጤስ ሰዎች ሁልጊዜ ውሸታሞች፥ ክፉ አውሬዎች፥ ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው” ብሎአል። 13ይህም ምስክርነት እውነት ነው፤ ስለዚህ የተሟላ እምነት እንዲኖራቸው እነዚህን ሰዎች ገሥጻቸው። 14የአይሁድን ተረት እንዳይከተሉና እውነትን የሚቃወሙትን ሰዎች ትእዛዝ እንዳይሰሙ በብርቱ ገሥጻቸው። 15ለንጹሖች፥ ሁሉ ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኩሶችና ለማያምኑ ሰዎች ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም፤ እንዲያውም አእምሮአቸውም ሆነ ኅሊናቸው የረከሰ ነው። 16“እግዚአብሔርን እናውቃለን” ይላሉ፤ በሥራቸው ግን ይክዱታል፤ እነርሱ አጸያፊዎች፥ የማይታዘዙና ምንም መልካም ሥራ ማድረግ የማይችሉ ናቸው።
Currently Selected:
ወደ ቲቶ 1: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997