መኃልየ መኃልይ 4
4
ሙሽራው
1ፍቅሬ ሆይ! እንዴት ውብ ነሽ!
እንዴት ያማርሽ ነሽ!
ዐይኖችሽ በፊትሽ መሸፈኛ ዐይነ ርግብ ውስጥ ሲታዩ
እንደ ርግብ ያማሩ ናቸው፤
ጠጒርሽ ከገለዓድ ተራራ ላይ እንደሚወርድ
የፍየል መንጋ ነው።
2ጥርሶችሽ፥ በመካከላቸው ምንም መኻን
ሳይኖርባቸው መንታ መንታ እንደሚወልዱ፥
ተሸልተው በውሃ እንደ ታጠቡ፥
ነጫጭ የበጎች መንጋ ደስ ያሰኛሉ።
3ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ያማሩ ናቸው፤
ስትነጋገሪም እጅግ ደስ ያሰኛሉ፤
ሁለቱ ጒንጮችሽ በፊትሽ መሸፈኛ ዐይነ ርግብ ውስጥ ሲታዩ
ለሁለት የተከፈለ የሮማን ፍንካች ይመስላሉ።
4አንገትሽ በሺህ የሚቈጠሩ የኀያላን ጋሻዎችና
የጦር ዕቃዎች ተሰቅለው የሚታዩበትን፥
የጦር ምሽግ ይሆን ዘንድ የተሠራውን
የዳዊትን ግንብ ይመስላል።
5ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ ሆነው የተወለዱና
በሱፍ አበባዎች መካከል የተሰማሩ
የዋልያ ግልገሎችን ይመስላሉ።
አራተኛ መዝሙር
የጋብቻ ኅብረት
6ሌሊቱ እስከሚነጋና
ጨለማውም እስከሚያልፍ ድረስ
ወደ ከርቤ ተራራና
ወደ ዕጣን ኮረብታ ሄጄ ዐርፋለሁ።
7ፍቅሬ ሆይ! ሁለንተናሽ ውብ ነው፤
ምንም እንከን የለብሽም።
8ሙሽራዬ ሆይ! ከሊባኖስ ወደ እኔ ነይ፤
ከሊባኖስ ወደ እኔ ነይ፤
ከአማና ተራራ ጫፍ ውረጂ፤
የአንበሳና የነብር መኖሪያ ከሆኑት
ከሠኒርና ከሔርሞን ተራራዎች ወርደሽ ነይ
9ውድ እኅቴ የሆንሽ ሙሽራዬ ሆይ፥
የዐይኖችሽ አመለካከትና የአንገትሽ ድሪ
ልቤን ማርኮታል፤
10ውድ እኅቴ የሆንሽ ሙሽራዬ ሆይ፥
ፍቅርሽ እንዴት ያስደስታል!
ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ ደስ ያሰኛል፤
የሽቶሽ መዓዛ ከማንኛውም ሽቶ ይበልጣል።
11ሙሽራዬ ሆይ! ከከንፈሮችሽ የማር ወለላ ይፈስሳል፤
ከአንደበትሽም ማርና ወተት ይፈልቃል፤
የልብስሽም መዓዛ እንደ ሊባኖስ ሽቱ ነው።
12አንቺ የእኔ ሙሽራ፥
እንደ አትክልት ቦታና
ለሌሎች እንደ ተዘጋ ምንጭ ነሽ።
13የአንቺ መተላለፊያ በጣፋጭ ፍሬዎች እንደ ተሞላ
እንደ ሮማን የአትክልት ቦታ ነው።
14ናርዶስ፥ ቀጋ፥ ጠጅ ሣርና ቀረፋ፥
እንዲሁም ሽታቸው እንደ ዕጣን መዓዛ ያላቸው
ልዩ ልዩ ተክሎች ይገኙባታል፤
እንዲሁም ከርቤ፥ የሬት አበባና
ልዩ ልዩ የቅመማቅመም ተክሎች ይበቅሉባታል።
15አንቺ የአትክልት ቦታን እንደምታጠጣ ምንጭ ነሽ፤
የሕይወት ውሃም እንደሚገኝባት ጒድጓድ ነሽ፤
ከሊባኖስ ተራራ ሥር እንደሚፈልቅ ወንዝ ነሽ።
ሙሽራይቱ
16የሰሜን ነፋስ ሆይ! ንቃ!
አንተም የደቡብ ነፋስ ሆይ! ወደዚህ ና!
በአትክልት ቦታዬም ላይ ንፈስ፤
ዐየሩም በመልካም ሽታ የተሞላ ይሁን፤
ውዴም ወደ አትክልት ቦታው ይምጣ፤
ምርጥ የሆኑትንም ፍሬዎች ይመገብ።
Currently Selected:
መኃልየ መኃልይ 4: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997