YouVersion Logo
Search Icon

ወደ ሮም ሰዎች 15

15
ሰዎችን ማስደሰት እንደሚገባ
1እኛ በእምነት ብርቱዎች የሆንን፥ የደካሞችን ድካም መሸከም ይገባናል እንጂ ራሳችንን ብቻ የምናስደስት መሆን የለብንም፤ 2እያንዳንዳችን ሌላው ሰው በእምነቱ እንዲጠነክር እርሱን የሚጠቅመውንና የሚያስደስተውን ነገር እናድርግ። 3ክርስቶስ ራሱን አላስደሰተም፤ ይልቁንም “ሰዎች አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ወረደ” የሚለው የቅዱሳት መጻሕፍት አባባል ደረሰበት። #መዝ. 69፥9። 4ከቅዱሳት መጻሕፍት በምናገኛቸው ትዕግሥትና መጽናናት ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብለው የተጻፉት ሁሉ ትምህርት እንዲሆኑን ተጽፈዋል። 5የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እርስ በርሳችሁ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል አብሮ የመኖርን ኅብረት ይስጣችሁ። 6እንዲሁም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር በአንድ ልብና በአንድ ቃል እንድታከብሩት ያድርጋችሁ።
የወንጌል ቃል ለአሕዛብ እንደ ተሰበከ
7ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እናንተን እንደ ተቀበላችሁ እናንተ ሁላችሁም አንዱ ሌላውን በደስታ ይቀበለው። 8ይህንንም ስናገር እግዚአብሔር ለቀደሙት አባቶች የሰጠው ተስፋ እንዲፈጸምና የእግዚአብሔርም እውነተኛነት እንዲታወቅ ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ ሆነ ማለቴ ነው። 9ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ የሆነበትም ሌላው ምክንያት አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ እንዲያመሰግኑት ነው፤ ይህም፦
“ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤
ለስምህም በዝማሬ ምስጋና አቀርባለሁ”
ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። #2ሳሙ. 22፥50፤ መዝ. 18፥49። 10ደግሞም፥
“እናንተ አሕዛብ፥
ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ደስ ይበላችሁ!” ተብሎ ተጽፎአል። #ዘዳ. 32፥43።
11እንደገናም፦
“አሕዛብ ሁሉ! ጌታን አመስግኑት፤
ሕዝቦች ሁሉ አመስግኑት!” ተብሎ ተጽፎአል። #መዝ. 117፥1።
12እንዲሁም ኢሳይያስ፦
“ከእሴይ ዘር የሚወለድ ይመጣል፤
የአሕዛብም መሪ ለመሆን ይነሣል፤
እነርሱም ተስፋቸውን በእርሱ ላይ ያደርጋሉ” ይላል። #ኢሳ. 11፥10።
13ተስፋችሁ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል እያደገ እንዲሄድ የተስፋ አምላክ በእርሱ በመታመናችሁ ደስታንና ሰላምን በሙላት ይስጣችሁ።
ጳውሎስ በድፍረት የጻፈበት ምክንያት
14ወንድሞቼ ሆይ! በደግነት የተሞላችሁ፥ በዕውቀት የበለጸጋችሁና እያንዳንዳችሁም ሌላውን ለመምከር የምትችሉ መሆናችሁን ተረድቼአለሁ። 15አንዳንድ ነገሮችን ላስታውሳችሁ ፈልጌ ይህን መልእክት እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት በድፍረት ጻፍኩላችሁ። 16ይህም ጸጋ የተሰጠኝ የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለአሕዛብ በማብሠር እንደ ካህን ሆኜ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ስለዚህ አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰና እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ አገለግላለሁ። 17በዚህ ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ለማገልገል በመቻሌ እመካለሁ። 18አሕዛብ ታዛዦች እንዲሆኑ ለማድረግ ክርስቶስ በእኔ ቃልና ሥራ አማካይነት የሠራው ነገር ካልሆነ በቀር ምንም ነገር ለመናገር አልደፍርም። 19እንዲሁም በታላላቅ ተአምራትና በድንቅ ሥራዎች፥ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ከኢየሩሳሌምና ከአካባቢዋ ጀምሮ እስከ እልዋሪቆን ድረስ የክርስቶስን ወንጌል አስተምሬአለሁ።
20የዘወትር ምኞቴም ሌላው ሰው በጣለው መሠረት ላይ መገንባት ሳይሆን የክርስቶስ ስም ባልተሰማበት ስፍራ ሁሉ መልካሙን ዜና ማብሠር ነው። 21ይህም፦
“ከዚህ በፊት ስለ እርሱ ምንም ያልተነገራቸው ሰዎች ያያሉ፤
ስለ እርሱ ያልሰሙም ያስተውላሉ”
ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።
ጳውሎስ ወደ ሮም ለመሄድ እንደ ዐቀደ
22እስከ አሁን ወደ እናንተ ለመምጣት ያልቻልኩት ቀደም ብዬ በተናገርኩት ምክንያት ነው። #ሮም 1፥13። 23አሁን ግን በዚህ አካባቢ ባሉት አገሮች የምሠራባቸው ቦታዎች ስለሌሉ፥ እንዲሁም ከብዙ ዓመቶች ጀምሬም እናንተን ለመጐብኘት ከፍ ያለ ምኞት ስላለኝ 24ወደ እስፔን በምሄድበት ጊዜ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁ ዐቅጃለሁ። ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ደስ ብሎኝ ከቈየሁ በኋላ ጒዞዬን ለመቀጠል የሚያስችለኝን ርዳታ እንደምታደርጉልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። 25አሁን ግን ለእግዚአብሔር ወገኖች የሚሰጥ የገንዘብ ርዳታ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ። 26ይኸውም የመቄዶንያና በአካይያ የሚገኙ የእግዚአብሔር ወገኖች በኢየሩሳሌም ላሉት ድኾች የገንዘብ ርዳታ ለመላክ በፈቃዳቸው ስለ ወሰኑ ነው። #1ቆሮ. 16፥1-4። 27ይህንንም ርዳታ በፈቃደኛነት የለገሡት ግዴታቸው በመሆኑ ነው፤ አሕዛብ ከአይሁድ ጋር የመንፈስ በረከት ተካፋዮች ከሆኑ እነርሱም በሥጋዊ በረከታቸው አይሁድን የመርዳት ግዴታ አለባቸው። #1ቆሮ. 9፥11። 28ስለዚህ ይህን የተሰበሰበውን የገንዘብ ርዳታ ወደ ኢየሩሳሌም ወስጄ የማስረከብ ሥራዬን ከፈጸምኩ በኋላ በእናንተ በኩል አድርጌ ወደ እስፔን እሄዳለሁ። 29ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜም የክርስቶስን በረከት በሙላት ይዤላችሁ እንደምመጣ ዐውቃለሁ።
30ወንድሞቼ ሆይ! ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ በትግሌ እንድትረዱኝ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር እለምናችኋለሁ። 31የምትጸልዩልኝም በይሁዳ ምድር ካሉት ከማያምኑ ሰዎች እጅ እንድድንና በኢየሩሳሌም ያለኝ አገልግሎትም በእግዚአብሔር ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ነው። 32ይህም ከሆነ በኋላ የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆን በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር ማረፍ እወዳለሁ። 33የሰላም አምላክ ከሁላችሁም ጋር ይሁን! አሜን።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in