YouVersion Logo
Search Icon

የዮሐንስ ራእይ 1

1
1ይህ ራእይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ እንዲያሳያቸው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም መልአኩን ልኮ ለአገልጋዩ ለዮሐንስ ይህን ራእይ ገለጠለት። 2ዮሐንስም ስለ እግዚአብሔር ቃልና ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አስተማረው እውነት፥ እንዲሁም ስላየውም ነገር ሁሉ መሰከረ። 3ይህ ሁሉ የሚፈጸምበት ጊዜ ቅርብ ስለ ሆነ ይህን የትንቢት ቃል የሚያነብ የተባረከ ነው! እንዲሁም የትንቢቱን ቃል የሚሰሙና በትንቢቱም ውስጥ የተጻፈውን የሚፈጽሙ የተባረኩ ናቸው።
ለሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያን የተላከ ሰላምታ
4-5ከዮሐንስ ለሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያን።
ካለው፥ ከነበረውና፥ ከሚመጣው ከእግዚአብሔር፥ በዙፋኑ ፊት ካሉት ከሰባቱ መንፈሶች፥ እንዲሁም ከሞት በመነሣት በኲር ከሆነው የምድር ነገሥታት ገዢ፥ ታማኝ ምስክር ከሆነው፥ ከሚወደንና በደሙ ከኃጢአታችን ነጻ ካወጣን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። #ዘፀ. 3፥14፤ ራዕ. 4፥5። #ኢሳ. 55፥4፤ መዝ. 89፥27። 6የኢየሱስ ክርስቶስን አባት እግዚአብሔርን እንድናገለግል ንጉሦችና ካህናት ላደረገን፥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ኀይል ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይሁን! አሜን። #ዘፀ. 19፥6፤ ራዕ. 5፥10።
7እነሆ በደመና ይመጣል፤ የወጉት ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ሰው ሁሉ ያየዋል፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ምክንያት ያለቅሳሉ፤ ይህ ነገር እውነት ነው፤ አሜን። #ዳን. 7፥13፤ ማቴ. 24፥30፤ ማር. 13፥26፤ ሉቃ. 21፥27፤ 1ተሰ. 4፥17፤ ዘካ. 12፥10፤ ዮሐ. 19፥34፤37።
8ያለው፥ የነበረው፥ የሚመጣውም ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር “አልፋና ዖሜጋ፥ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ!” ይላል። #ራዕ. 22፥13፤ ዘፀ. 3፥14።
የክርስቶስ በራእይ መገለጥ
9በኢየሱስ ክርስቶስ የመከራውና የመንግሥቱ እንዲሁ የትዕግሥቱ ከእናንተ ጋር ተካፋይ የሆንኩ እኔ ወንድማችሁ ዮሐንስ በእግዚአብሔር ቃልና በኢየሱስ ምስክርነት ምክንያት ታስሬ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርኩ፤ 10በጌታ ቀን በመንፈስ ተመስጦ ላይ ሳለሁ የእምቢልታ ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ከበስተኋላዬ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ 11“የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያን፥ ማለትም ወደ ኤፌሶን፥ ወደ ሰምርኔስ፥ ወደ ጴርጋሞን፥ ወደ ትያጥሮን፥ ወደ ሰርዴስ፥ ወደ ፊላደልፍያና ወደ ሎዶቅያ ላክ።”
12ማን እንደ ተናገረኝ ለማወቅ ወደ ኋላዬ ዞር አልኩ፤ ዞር ባልኩ ጊዜም ሰባት የወርቅ መቅረዞችን አየሁ፤ 13በመቅረዞቹ መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፤ እርሱ እስከ እግሩ የሚደርስ ረጅም ልብስ የለበሰ፥ ደረቱን በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበረ። #ዳን. 7፥13፤ 10፥5። 14ራሱና የራስ ጠጒሩ በረዶን እንደሚመስል ሱፍ ነጭ ነበር፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤ #ዳን. 7፥9፤ 10፥6። 15እግሮቹም በእሳት ፍም ውስጥ እንደ ነጠረ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ታላቅ የፏፏቴ ውሃ ድምፅ ነበረ፤ #ሕዝ. 1፥24፤ 43፥2። 16በቀኝ እጁ ሰባት ኮከቦችን ይዞ ነበር፤ በሁለት በኩል ስለት ያለው ሰይፍ ከአፉ ይወጣ ነበር፤ ፊቱም በሙሉ ድምቀቱ እንደሚያበራ ፀሐይ ነበረ። 17ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ በእግሩ ሥር ወደቅኩ፤ እርሱ ግን ቀኝ እጁን በላዬ ጭኖ እንዲህ አለኝ፤ “አትፍራ፤ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ፤ #ኢሳ. 44፥6፤ 48፥12፤ ራዕ. 2፥8፤ 22፥13። 18እኔም ሕያው ነኝ፤ ሞቼ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ፥ ለዘለዓለም ሕያው ነኝ፤ በሞትና በሲኦል ላይ ሥልጣን አለኝ። 19እንግዲህ ያየኸውን፥ አሁን ያለውንና በኋላ የሚመጣውን ጻፍ። 20በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ኮከቦችና የሰባቱም የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ኮከቦች የሰባቱ አብያተ ክርስቲያን መላእክት ናቸው፤ ሰባቱ መቅረዞችም ሰባት አብያተ ክርስቲያን ናቸው።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in