YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 85

85
ስለ ሕዝብ ሰላም የሚቀርብ ጸሎት
1እግዚአብሔር ሆይ!
ለምድርህ ምሕረትን አሳየህ፤
የያዕቆብን ዘር እንደገና አበለጸግህ።
2የሕዝብህን በደል ይቅር አልክ፤
ኃጢአታቸውንም ሁሉ ደመሰስክ።
3እነርሱን ከመቈጣት ታገሥህ፤
ብርቱ ቊጣህንም መለስህ።
4አዳኛችን እግዚአብሔር ሆይ!
ከተሰደድንበት መልሰን፤
በእኛም ላይ ያለህን ቅርታ አርቅልን።
5በእኛ ላይ የምትቈጣው ለዘለዓለም ነውን?
ቊጣህንስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ታስተላልፋለህን?
6እኛ ሕዝብህ በአንተ እንደሰት ዘንድ፥
እንደገና ሕይወትን አትዘራብንምን?
7እግዚአብሔር ሆይ!
ዘለዓለማዊ ፍቅርህን አሳየን፤ አድነንም።
8እግዚአብሔር አምላክ የሚናገረውን ቃል ልስማ፤
እንደገና በስሕተት መንገድ ካልሄዱ በቀር፥
ለሕዝቡና ለታማኞቹ ሰላምን እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጥቶአል።
9ክብሩ በምድራችን ይኖር ዘንድ፥
እርሱን ለሚፈሩት አዳኝነቱ ቅርብ ነው።
10ፍቅርና እውነት ይተቃቀፋሉ፤
ጽድቅና ሰላም ይስማማሉ።
11የሰው ታማኝነት ከምድር ይፈልቃል
ጽድቅም ከሰማይ ወደ ታች ይመለከታል።
12እግዚአብሔር ያበለጽገናል፤
ምድራችንም ብዙ የመከር ፍሬ ትሰጠናለች።
13ፈለጉን እንከተል ዘንድ
ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት ይሄዳል።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in