YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ መዝሙር 78

78
እግዚአብሔርና ሕዝቡ
1ሕዝቤ ሆይ! ትምህርቴን አድምጥ፤
ቃሌንም በጥንቃቄ ስማ፤
2ንግግሬን በምሳሌ እጀምራለሁ፤
ከጥንት ጀምሮ የተሰወረውን ምሥጢር እገልጣለሁ። #ማቴ. 13፥35።
3ስለ ሰማናቸውና ስለ ዐወቅናቸው፥
አባቶቻችንም ስለ ነገሩን ነገሮች እናገራለሁ፤
4እነዚህን ነገሮች ከልጆቻችን አንሰውርም፤
ስለ እግዚአብሔር ኀይል፥
ስላከናወናቸውም ታላላቅ ሥራዎችና ስላደረጋቸው ድንቅ ነገሮች
ለተከታዩ ትውልድ እንናገራለን።
5እርሱ ሥርዓትን ለያዕቆብ ልጆች ዐወጀ፤
ለእስራኤልም ሕግን መሠረተ፤
ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ የቀድሞ አባቶቻችንን አዘዛቸው።
6ይህንንም ያደረገው ተከታዩ ትውልድ
እንዲያውቀውና ለልጆቹም እንዲያስተምረው ነው።
7በዚህ ዐይነት እነርሱም በእግዚአብሔር ላይ ይታመናሉ፤
ትእዛዞቹንም ዘወትር ይፈጽማሉ እንጂ
ያደረገውን ሁሉ አይረሱም።
8እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ዐመፀኞችና እምቢተኞች አይሆኑም፤
እነዚያ እግዚአብሔርን በማመን የጸኑ አልነበሩም፤
ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው አልኖሩም።
9የኤፍሬም ልጆች ቀስትና ፍላጻ ይዘው ሳለ
በጦርነት ቀን ሸሹ።
10ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤
ሕጉንም ለመፈጸም እምቢ አሉ።
11ያሳያቸውን ተአምራት ሁሉ እና
ያደረገውን መልካም ነገር ሁሉ ረሱ።
12በግብጽ አገር በጾዓን ሜዳ የቀድሞ አባቶቻቸው እያዩ
እግዚአብሔር በፊታቸው ተአምራትን አደረገ። #ዘፀ. 7፥8—12፥32።
13ባሕሩን ከፍሎ በመካከሉ አሳለፋቸው፤
ውሃው እንደ ግንብ እንዲቆም አደረገ። #ዘፀ. 14፥21-22።
14ቀን በደመና፥ ሌሊት በእሳት ብርሃን መራቸው። #ዘፀ. 13፥21-22።
15በበረሓ አለቱን ሰነጠቀ፤
ከዚያም ከጥልቅ ባሕር የሚገኘውን ያኽል ብዙ ውሃ ሰጣቸው። #ዘፀ. 17፥1-7፤ ዘኍ. 20፥2-13።
16ምንጭን ከአለት አፈለቀ፤
ውሃውም እንደ ወንዝ እንዲፈስስ አደረገ።
17እነርሱ ግን እግዚአብሔርን በመበደል ኃጢአት መሥራት ቀጠሉ፤
በበረሓም በልዑል እግዚአብሔር ላይ ዐመፁ።
18የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ
ሆን ብለው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት። #ዘፀ. 16፥2-15፤ ዘኍ. 11፥4-23፤31-35።
19እንዲህ እያሉም በእግዚአብሔር ላይ አጒረመረሙ፤
“እግዚአብሔር በበረሓ ማእድ ዘርግቶ ምግብ ሊሰጥ ይችላልን?
20አለቱን መሰንጠቁና ውሃም እንደ ጐርፍ ማፍሰሱ እውነት ነው፤
ታዲያ፥ ምግብን ሊሰጠን፥ ሥጋንም ሊያዘጋጅልን ይችላል ማለት ነውን?”
21እግዚአብሔር ይህን በሰማ ጊዜ በጣም ተቈጣ፤
በያዕቆብ ልጆች ላይ እሳቱ ነደደ፤
በእስራኤልም ላይ ቊጣው ተቀጣጠለ።
22ይህም የሆነው በእርሱ ስላላመኑና
እንደሚያድናቸውም ስላልተማመኑበት ነው።
23ሆኖም ከላይ ያሉትን ሰማያትን አዘዘ፤
የሰማይንም በሮች ከፈተ።
24ይበሉት ዘንድ ለሕዝቡ መናን አዘነበላቸው፤
የሰማይንም ምግብ ሰጣቸው። #ዮሐ. 6፥31።
25በዚህ ዐይነት ሰዎች የመላእክትን እንጀራ በሉ፤
እግዚአብሔር የሚፈልጉትን ምግብ ሁሉ ሰጣቸው።
26የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤
በኀይሉም የደቡብን ነፋስ አንቀሳቀሰ።
27ብዙ ሥጋ እንደ አፈር፥
ብዙ ድርጭቶችንም እንደ ባሕር አሸዋ
ለሕዝቡ አዘነበላቸው።
28በሰፈራቸው መካከል በድንኳኖች ዙሪያ
ድርጭቶችን አወረደላቸው።
29ስለዚህ ሕዝቡ በልተው ጠገቡ፤
እግዚአብሔር የተመኙትን ሁሉ ሰጣቸው።
30ይህም ሁሉ ሆኖ መጐምጀታቸው ሳይገታና
ምግባቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥
31የእግዚአብሔር ቊጣ በእነርሱ ላይ ተነሣ፤
የእስራኤልን ኀያላን ሰዎች ገደለ፤
ምርጥ ወጣቶችንም በአጭሩ ቀጨ።
32ይህም ሁሉ ሆኖ ሕዝቡ ኃጢአት ከመሥራት ገና አልተገታም፤
ብዙ ተአምራት ቢያሳያቸውም በእርሱ አላመኑም።
33ስለዚህ ዕድሜአቸውን እንደ እስትንፋስ አሳጠረ፤
ሕይወታቸውም በሽብር እንዲያልቅ አደረገ።
34ከእነርሱ ጥቂቶቹን በሞት በቀጣበት ጊዜ
የቀሩት ወደ እርሱ ይመለሱ ጀመር፤
ንስሓ ገብተውም ወደ እርሱ ከልባቸው ይመለሳሉ።
35እግዚአብሔር አምባቸው እንደ ሆነ ያስታውሳሉ፤
ልዑል እግዚአብሔርም አዳኛቸው እንደ ሆነ ያስባሉ።
36ነገር ግን በቃላቸው ሸነገሉት፤
የሚናገሩትም ሁሉ ሐሰት ነበር።
37ለእርሱ ታማኞች አልነበሩም፤
የእርሱንም ቃል ኪዳን አላከበሩም።
38ሆኖም እግዚአብሔር ለሕዝቡ ምሕረትን አደረገ፤
ኃጢአታቸውን ይቅር አላቸው እንጂ አላጠፋቸውም።
ብዙ ጊዜ ቊጣውን መለሰ፤
ብዙ ጊዜም መዓቱን ገታ።
39ካለፈ በኋላ እንደማይመለስ ነፋስ፥
ሟች ፍጥረቶች መሆናቸውን አስታወሰ።
40በበረሓ ሳሉ ብዙ ጊዜ በእርሱ ላይ ዐመፁ፤
በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ አሳዘኑት።
41በመደጋገም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤
የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት።
42እነርሱን ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀንና
ታላቅ ኀይሉን አላስታወሱም።
43በግብጽ አገር በጾዓን ሜዳ ያደረጋቸውን ታላላቅ
ሥራዎችና ተአምራቱን ዘነጉ።
44የወንዞቻቸውን ውሃ ወደ ደም ለወጠ፤
ስለዚህ ግብጻውያን ከወንዞቻቸው ውሃ መጠጣት አልቻሉም። #ዘፀ. 7፥17-21።
45እነርሱን የሚያሠቃዩ ዝንቦችንና
ጥፋትን የሚያስከትሉ እንቊራሪቶችን ወደ እነርሱ ላከ። #ዘፀ. 8፥1-6፤ 20፥24።
46ሰብላቸውን ለኩብኩባ፥
ምርታቸውንም ለአንበጣ ሰጠ። #ዘፀ. 10፥12-15።
47የወይን ተክሎቻቸውን በበረዶ፥
የበለስ ዛፎቻቸውንም በውርጭ አጠፋ።
48ከብቶቻቸውን በበረዶ፥
በጎቻቸውንም በመብረቅ ገደለ። #ዘፀ. 9፥22-25።
49የጥፋት መልእክተኞች ቡድን የሆኑትን አስፈሪውንና
ኀይለኛ ቊጣውን፥ ማዋረዱንና ማስጨነቁን ላከባቸው።
50ለቊጣው መንገድን አዘጋጀ፤ ከሞትም አላዳናቸውም፤
ነገር ግን ለመቅሠፍት አሳልፎ ሰጣቸው።
51የካምን ልጆች የመጀመሪያ የወንድነት ፍሬ፥
በግብጽ በኲሮችን ሁሉ ገደለ። #ዘፀ. 12፥29።
52ሕዝቡን አውጥቶ እንደ በጎች አሰማራቸው፤
በበረሓም እንደ በግ መንጋ መራቸው። #ዘፀ. 13፥17-22።
53በሰላም ስለ መራቸው አልፈሩም፤
ነገር ግን ባሕሩ ተጥለቅልቆ
ጠላቶቻቸውን አሰጠማቸው። #ዘፀ. 14፥26-28።
54ወደ ተቀደሰችው ምድሩ፥
በኀይሉ ወደያዛት ወደ ተራራማዋ አገር አመጣቸው። #ዘፀ. 15፥17፤ ኢያሱ 3፥14-17።
55ከእነርሱ በፊት አሕዛብን አባረረ፤
ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ነገዶች አከፋፈለ፤
ቤቶቻቸውንም ለራሱ ሕዝብ ሰጠ። #ኢያሱ 11፥16-23።
56የእርሱ ሕዝቦች ግን በልዑል እግዚአብሔር ላይ ዐመፁ፤
ተፈታተኑትም፤ ትእዛዞቹንም አልፈጸሙም። #መሳ. 2፥11-15።
57ይልቁንም እንደ አባቶቻቸው ዐመፀኞችና ከዳተኞች ሆኑ፤
እንደ ተጣመመ ፍላጻ የማያስተማምኑ ሆኑ።
58የአሕዛብ አምልኮ በሚፈጽሙባቸው
ስፍራዎቻቸው እግዚአብሔርን አስቈጡት፤
በጣዖቶቻቸውም አስቀኑት።
59እግዚአብሔርም በሰማ ጊዜ ተቈጣ፤
ሕዝቡንም ፈጽሞ ተዋቸው።
60በሴሎ በሰዎች መካከል ይኖርባት የነበረችውን ድንኳኑን ተዋት። #ኢያሱ 18፥1፤ ኤር. 7፥12-14፤ 26፥6።
61የኀይሉና የክብሩ መታወቂያ ምልክት የነበረችውን የቃል ኪዳን ታቦት፥
ጠላቶች ማርከው እንዲወስዱአት አደረገ። #1ሳሙ. 4፥4-22።
62የራሱን ሕዝብ ተቈጣ፤
በሰይፍ እንዲገደሉም አደረገ።
63ጐልማሶች ሁሉ በእሳት ተቃጥለው ሞቱ፤
ልጃገረዶችም የጋብቻቸውን ደስታ ሳያዩ ተቀጩ።
64ካህናት ሁሉ በሰይፍ ተገደሉ፤
ሚስቶቻቸውም ሊያለቅሱላቸው አልቻሉም።
65በመጨረሻም እግዚአብሔር ከእንቅልፍ
እንደሚነቃ ሰው ተነሣ፤
የወይን ጠጅ ጠጥቶ ድፍረት እንደሚሰማው ጀግና ሆነ።
66ጠላቶቹ ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዲሸሹና
ዘለዓለማዊ ኀፍረት እንዲከናነቡ አደረገ።
67የዮሴፍን ተወላጆች ናቀ፤
የኤፍሬምንም ነገድ አልመረጠም።
68ነገር ግን የይሁዳን ነገድና
በጣም የሚወዳትን የጽዮንን ተራራ መረጠ።
69በዚያም በሰማይ ያለውን ቤቱን የምትመስለውን መቅደሱን ሠራ፤
ለዘለዓለም የምትኖርና እንደ ምድር የጸናች አደረጋት።
70ባሪያውን ዳዊትን መረጠ፤
ከበጎች መሰማሪያም ወሰደው፤ #1ሳሙ. 16፥11-12፤ 2ሳሙ. 7፥8፤ 1ዜ.መ. 17፥7።
71ከበጎች እረኝነት አውጥቶም፥
የእስራኤል ንጉሥና የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠባቂ አደረገው።
72ዳዊትም በፍጹም ቅንነት ጠበቃቸው፤
በጥበብም መራቸው።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for መጽሐፈ መዝሙር 78