መጽሐፈ መዝሙር 76
76
የእግዚአብሔር ድል አድራጊነት
1እግዚአብሔር በይሁዳ የታወቀ ነው፤
ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው።
2ቤቱን በሳሌም (ኢየሩሳሌም) አደረገ፤
በጽዮንም ተራራ ላይ ይኖራል።
3በዚያም የሚያንጸባርቁ ፍላጻዎችን፥ ጋሻና ጦርን፥
ሌሎችንም የጦር መሣሪያዎች ሁሉ ሰባበረ።
4አምላክ ሆይ አንተ አስፈሪ ነህ፤
ግርማህም ከታላላቅ ተራራዎች በላይ ነው።
5ጀግኖች ወታደሮች የማረኩትን ተቀሙ፤
እጃቸውንም ማንሣት አቅቶአቸው
የመጨረሻ እንቅልፍ አንቀላፉ
6የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥
አንተ በገሠጽካቸው ጊዜ
ፈረሰኞች ከነፈረሶቻቸው ሞቱ።
7እግዚአብሔር ሆይ
አንተ ግን በሁሉ ዘንድ የተፈራህ ነህ፤
አንተ ስትቈጣ በፊትህ የሚቆም አንድ እንኳ አይኖርም፤
8ፍርድህን ከሰማይ እንዲታወቅ ስታደርግ
ምድሪቱ ፈርታ ጸጥ አለች፤
9አንተ በምድር የተጨቈኑትን ሁሉ ለመቤዠት፥
ለፍርድ በተነሣህ ጊዜ ዓለም ጸጥ አለ።
10የሰው ቊጣ አንተን ያመሰግንሃል፤
ከጦርነት የተረፉትም በዓልህን ያከብራሉ።
11መፈራት ለሚገባው ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ ተስላችሁ
የተሳላችሁትን ስእለት ፈጽሙ፤
እናንተ በቅርብ ያላችሁ ሕዝቦች
መባ አምጡለት።
12ትዕቢተኞች የሆኑትን መሳፍንት ያዋርዳል፤
ታላላቅ ነገሥታትንም ያርበደብዳል።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 76: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997