መጽሐፈ መዝሙር 147
147
ለሁሉን ቻዩ አምላክ የሚቀርብ ምስጋና
1እግዚአብሔርን አመስግኑ!
ለአምላካችን የምስጋና መዝሙር ማቅረብ መልካም ነው፤
እርሱን ማመስገን ደስ የሚያሰኝና ተገቢ ነው።
2እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድሳል፤
ከእስራኤል የተሰደዱትንም ይመልሳል።
3ልባቸው የተሰበረባቸውን ይፈውሳል፤
ቊስላቸውንም ይጠግናል።
4የከዋክብትን ብዛት ቈጥሮ ያውቃል፤
እያንዳንዳቸውንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።
5አምላካችን ታላቅና ኀያል ነው፤
ለዕውቀቱም ወሰን የለውም።
6ትሑታንን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤
ክፉ አድራጊዎችን ግን በምድር ላይ ጥሎ ያዋርዳቸዋል።
7ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤
በገና እየደረደራችሁ ለአምላካችን ዘምሩ።
8እርሱ ደመናን በሰማይ ላይ ይዘረጋል፤
ለምድር ዝናብን ይሰጣል፤
ተራራዎችንም በለምለም ሣር ይሸፍናል።
9ለእንስሶች ምግብን ይሰጣል፤
ምግብ አጥተው የሚጮኹ
የቊራ ጫጩቶችንም ይመግባል።
10የእርሱ ደስታ በብርቱ ፈረሶችና፤
በጦረኞች ኀይል አይደለም።
11እርሱን ደስ የሚያሰኙት
በአክብሮት የሚፈሩትና በዘለዓለማዊ ፍቅሩ
የሚታመኑ ሰዎች ናቸው።
12ኢየሩሳሌም ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ!
ጽዮን ሆይ! አምላክሽን አመስግኚ!
13እርሱ የበሮችሽን መወርወሪያ አጠንክሮ ይጠብቃል፤
በውስጥሽ ያሉትንም ሕዝቦችሽን ይባርካል።
14እርሱ ወሰንሽን በሰላም ይጠብቃል፤
በመልካም ስንዴም ያጠግብሻል።
15ለምድር ትእዛዙን ያስተላልፋል፤
ቃሉም ወዲያው ይፈጸማል።
16ዐመዳዩን እንደ ባዘቶ ያነጥፈዋል፤
ውርጩንም እንደ ዐመድ ይበትነዋል።
17በረዶውንም እንደ ጠጠር አድርጎ ያወርደዋል፤
እርሱ የሚልከውን ውርጭ ማንም ሊቋቋመው
አይችልም።
18ከዚህ በኋላ ትእዛዝ ይሰጣል፤
የተጋገረውም በረዶ ይቀልጣል፤
ነፋስን ያነፍሳል፤ ውሃም ይፈስሳል።
19ቃሉን ለያዕቆብ ልጆች
ሕጉንና ሥርዓቱንም ለእስራኤል ይሰጣል።
20ይህን ሁሉ ለሌሎች ሕዝቦች አላደረገም፤
እነርሱ ሕጉንም አያውቁም።
እግዚአብሔር ይመስገን!
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 147: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997