YouVersion Logo
Search Icon

መጽሐፈ ነህምያ 9

9
እስራኤላውያን ኃጢአታቸውን መናዘዛቸው
1በዚሁ ወር በሃያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ስለ ኃጢአታቸው መጸጸታቸውንና ማዘናቸውን ለመግለጥም ማቅ ለብሰው፥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ጾሙ፤ 2ራሳቸውንም ከባዕዳን ሕዝቦች ሁሉ ለዩ፤ ከዚህም በኋላ ሁሉም ተነሥተው በመቆም፥ እነርሱና የቀድሞ አባቶቻቸው የሠሩትን ኃጢአት ሁሉ ተናዘዙ። 3እዚያው እንደ ቆሙም፥ የአምላካቸው የእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሦስት ሰዓት ሙሉ ተነበበላቸው፤ ሌላም ሦስት ሰዓት ኃጢአታቸውን በመናዘዝ፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።
4ለሌዋውያኑ መቆሚያ መድረክ ነበር፤ በዚያም ላይ ኢያሱ፥ ባኒ፥ ቃድሚኤል፥ ሸባንያ፥ ቡኒ፥ ሼሬብያ፥ ባኒና ከናኒ በመቆም፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ።
5ኢያሱ፥ ቃድሚኤል፥ ባኒ፥ ሐሸባንያ፥ ሼሬብያ፥ ሆዲያ፥ ሸባንያና ፐታሕያ ተብለው የሚጠሩት ሌዋውያን፦
“ተነሥታችሁ በመቆም ዘለዓለማዊውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ከምስጋናና ከበረከት ሁሉ በላይ፥
ከፍ ከፍ ይበል! በሉ” አሉአቸው።
የንስሓ ጸሎት
6ከዚህም ሁሉ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲሉ ጸለዩ፦
“እግዚአብሔር ሆይ፥ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤
ሰማያትን፥
የሰማያትንም ሰማያት ከነሠራዊታቸው፥
ምድርንና በእርስዋም ላይ የሚገኘውን ሁሉ፥
ባሕሮችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገኙትን ሁሉ፥
ፈጠርክ፤ ለሁሉም ሕይወትን ሰጠሃቸው፤
የሰማይ ሠራዊት ይሰግዱልሃል።
7የባቢሎን ክፍል ከሆነችው ዑር፥
አብራምን መርጠህ ያመጣኸው፥
ስሙንም አብርሃም ያልከው፥
አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ። #ዘፍ. 11፥31—12፥1፤ 17፥5።
8እርሱም ለአንተ ታማኝ እንደ ሆነ ተመልክተህ፥
ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳንን አደረግህ፤
ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥
ፈሪዛውያን፥ ኢያቡሳውያንና ጌርጌሳውያን የሚኖሩባትንም
የከነዓንን ምድር ለዘሮቹ
መኖሪያ ርስት አድርገህ ልትሰጠው ቃል ገባህለት፤
አንተ ታማኝ ስለ ሆንክ ቃል ኪዳንህን አጽንተህ ጠብቀሃል። #ዘፍ. 15፥18-21።
9“አንተ የቀድሞ አባቶቻችን በግብጽ
የደረሰባቸውን መከራ አየህ፤
ቀይ ባሕር አጠገብ ሆነው እንድትረዳቸው ያቀረቡትን ልመና ሰማህ። #ዘፀ. 3፥7፤ 14፥10-12።
10በግብጽ ንጉሥ ላይ በባለሥልጣኖቹና በምድሩ
በሚኖሩትም ሕዝብ ሁሉ ላይ
ድንቅ ተአምራትን ገልጠህ አሳየህ።
ይህንንም ያደረግኸው የቀድሞ አባቶቻችን
እንዴት እንደሚጨቈኑ በማየትህ ነው፤
ይህንንም በማድረግህ እስከ ዛሬ ድረስ
ዝናህ የገነነ ሆኖአል። #ዘፀ. 7፥8—12፥32።
11ባሕሩን በፊታቸው ለሁለት ከፈልክ፤
በደረቅ ምድርም ተሻገሩ፤
ድንጋይ ወደ ጥልቅ ባሕር እንደሚጣል፥
እነርሱን ያሳድዱ የነበሩትንም
ወደ ጥልቁ ጣልካቸው። #ዘፀ. 14፥21-29፤ 15፥4-5።
12በቀን በደመና ዐምድ መራሃቸው፤
በሌሊትም መንገዳቸውን በእሳት ዐምድ አበራህላቸው። #ዘፀ. 13፥21-22።
13ወደ ሲና ተራራ ወርደህ ከሰማይ
ሕዝብህን አነጋገርካቸው፤
ትክክለኛና ፍትሓዊ ሕግንና ሥርዓትን፥
መልካም የሆኑትን ደንቦችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው።
14የተቀደሰውን ሰንበትህንም እንዲያውቁ አደረግሃቸው፤
በአገልጋይህም በሙሴ አማካይነት
ትእዛዞችህን፥ ድንጋጌህንና ሕጎችህን ሰጠሃቸው። #ዘፀ. 19፥18—23፥33።
15“በተራቡም ጊዜ ምግብን ከሰማይ ሰጠሃቸው፤
በተጠሙም ጊዜ ውሃን ከአለት አፈለቅህላቸው፤
ለእነርሱ ልትሰጣቸው ቃል የገባህላቸውንም ምድር
በቊጥጥራቸው ሥር ያደርጉ ዘንድ አዘዝካቸው። #ዘፀ. 16፥4-15፤ 17፥1-7፤ ዘዳ. 1፥21።
16ነገር ግን የቀድሞ አባቶቻችን ትዕቢተኞችና እልኸኞች ሆኑ፤
ትእዛዞችህንም አልጠበቁም፤ #ዘኍ. 14፥1-4፤ ዘዳ. 1፥26-33።
17ታዛዦችም አልሆኑም።
በመካከላቸው ያደረግኸውን ተአምራት ሁሉ ረሱ፤
እልኸኞችም ሆነው፤
ወደ ግብጹ ባርነታቸው እንዲመልሳቸው
መሪ መረጡ።
አንተ ግን በፍቅር የተሞላህ፥
ለቊጣ የዘገየህ፥ ይቅር ባይ፥
ቸርና መሐሪ አምላክ በመሆንህ አልተውካቸውም። #ዘፀ. 34፥6፤ ዘኍ. 14፥18።
18በጥጃ አምሳል ለራሳቸው ጣዖትን ሠርተው፥
‘ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን አምላክ
ይህ ነው!’ አሉ፤
በአንተ ላይም ከፍተኛ የስድብን ቃል እንኳ ተናገሩ፤ #ዘፀ. 32፥1-4።
19ምሕረትህም ታላቅ በመሆኑ
በዚያ ምድረ በዳ ይጠፉ ዘንድ አልተውካቸውም፤
ነገር ግን የደመናው ዐምድ በቀን ይመራቸው ነበር፤
የእሳቱ ዐምድ በሌሊት ያበራላቸው ነበር።
20የሚያስተምራቸውን ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤
የሚመገቡትን መና፥ የሚጠጡትንም ውሃ ሰጠሃቸው።
21አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ ረዳሃቸው፤
ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ምንም አላሳጣሃቸውም፤
ልብሳቸው አላለቀም፤
እግራቸው አላበጠም።
22“የአሕዛብን መንግሥታትና ነገሥታትን ድል ነሥተው፥
ከምድራቸው አዋሳኞች የሆኑትን ጠረፎች እንዲይዙ አደረግህ፤
ሲሖን የተባለ ንጉሥ ይገዛት የነበረችውን
ሐሴቦን ተብላ የምትጠራውን ምድር፥
በድል አድራጊነት ያዙ፤
ዖግ የተባለው ንጉሥ ይገዛት የነበረችውንም የባሳንን ምድር ወረሱ። #ዘኍ. 21፥21-35።
23ብዛታቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የሆኑ ልጆችን ሰጠሃቸው፥
ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ
ቃል የገባህላቸውን ምድር፥
በድል አድራጊነት እንዲይዙ ፈቀድክላቸው። #ዘፍ. 15፥5፤ 22፥17፤ ኢያሱ 3፥14-17።
24ልጆቻቸው የከነዓንን ምድር ድል አድርገው ያዙ፤
በዚያ ይኖሩ የነበሩትንም ሕዝብ በፊታቸው ሆነህ አንተ ድል ነሣህላቸው፤
በነገሥታትና በዚያች የከነዓን አገር ሕዝብ ላይ
የፈለጉትን ሁሉ ያደርጉባቸው ዘንድ ኀይልን ሰጠሃቸው። #ኢያሱ 11፥23።
25የተመሸጉ ከተሞችንና፥ ለም የሆነችውን ምድር፤
በመልካም ነገር ሁሉ የተሟሉ ቤቶችን፥
የውሃ ጒድጐዶችንና የወይን ተክል ቦታዎችን
የወይራና ብዙ የፍሬ ዛፎችን ወረሱ፤
በልተው በመጥገብም ሰውነታቸውን አወፈሩ፤
በቸርነትህ በሰጠሃቸው መልካም ነገር ሁሉ ተደሰቱ። #ዘዳ. 6፥10-11።
26“ነገር ግን እነርሱ በአንተ ላይ ዐምፀው
ለቃልህ አንታዘዝም አሉ፤
ሕግህንም ላለመስማት ፊታቸውን መለሱ፤
በማስጠንቀቅ ወደ አንተ እንዲመለሱ
ያስተማሩአቸውን ነቢያትህን ገደሉ፤
በየጊዜውም በአንተ ላይ ክፉ የስድብ ቃል ተናገሩ፤
27ስለዚህም ጠላቶቻቸው እነርሱን ድል አድርገው
ይገዙአቸው ዘንድ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፤
እነርሱም አስጨነቁአቸው።
በችግራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፤
አንተም በሰማይ ሆነህ ሰማሃቸው፤
ከምሕረትህ ታላቅነት የተነሣ፥
ከጠላቶቻቸው የሚታደጉ መሪዎችን ላክህላቸው።
28ነገር ግን ሰላም ባገኙ ጊዜ
እንደገና ኃጢአት ሠሩ፤
አንተም እንደገና ድል ለሚነሡ ጠላቶቻቸው ተውካቸው
እነርሱም ገዙአቸው፤
ነገር ግን አንተ እንድትረዳቸው
እንደገና በጠየቁ ጊዜ
በሰማይ ሆነህ ሰማሃቸው፤
ከርኅራኄህም የተነሣ
በየጊዜው ታደግኻቸው። #መሳ. 2፥11-16።
29እነርሱም ወደ ሕግህ እንዲመለሱ
አስጠነቀቅኻቸው፤
በትዕቢታቸው ግን ትእዛዞችህን ናቁ፤
ቢፈጽሙአቸው ሕይወት በሚሰጡት ሕጎችህ ላይ ኃጢአት ሠሩ።
በልበ ደንዳናነት ፊታቸውን አዞሩ፤
በእልኸኛነታቸውም እምቢተኞች ሆኑ። #ዘሌ. 18፥5።
30አንተም ለብዙ ዓመቶች ታገሥካቸው፤
ያስተምሩአቸውም ዘንድ ነቢያትን በመንፈስህ አስነሣህላቸው፤
ነገር ግን እነርሱ አላዳመጡም፤
ስለዚህም ለጐረቤት ሕዝቦች ድል እንዲነሡአቸው
አሳልፈህ ሰጠሃቸው። #2ዜ.መ. 36፥15-16።
31እንደገናም ከምሕረትህ ታላቅነት የተነሣ አልተውካቸውም፤
አንተ ቸርና ይቅር ባይ አምላክም ስለ ሆንክ አልደመሰስካቸውም።
32“ቃል ኪዳንህንና ዘለዓለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ፥
ታላቁ፥ ኀያሉና አስፈሪው አምላካችን ሆይ!
በእኛ፥ በንጉሦቻችን፥ በመሪዎቻችን፥
በካህኖቻችን፥ በነቢዮቻችን፥
በቅድመ አያቶቻችን፥
እንዲሁም በሕዝብህ ሁሉ ላይ፥
ከአሦር ነገሥታት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥
የደረሰውን መከራ ሁሉ አስብ። #2ነገ. 15፥19፤29፤ 17፥3-6፤ ዕዝ. 4፥2፤10።
33እኛን ለመቅጣት ያደረግኸው ውሳኔ ትክክል ነው፤
እኛ በደል ብንሠራም፥ አንተ በታማኝነትህ እንደ ጸናህ ነህ።
34የቀድሞ አባቶቻችን፥ ንጉሦቻችን፥
መሪዎቻችንና ካህኖቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤
የሰጠሃቸውን ትእዛዞች ማስጠንቀቂያዎች አላዳመጡም።
35መንግሥታቸው በሰጠሃቸው ቸርነት፥
በሰጠሃቸው ሰፊና ለም መሬት፥
ይደሰቱ በነበረ ጊዜ እንኳ፥
አንተን አላመለኩም፥
ከኃጢአታቸውም አልተመለሱም።
36ስለዚህም አንተ ለአባቶቻችን ፍሬዋን እንዲበሉና በመልካም ነገሮችም እንዲደሰቱ፥
በሰጠሃቸው ምድር ላይ
እነሆ፥ ዛሬ እኛ ባሪያዎች ሆነናል።
37እኛም ኃጢአት በመሥራታችን ምክንያት ስላሳዘንክ፥
የምድሪቱንም በረከት በእኛ ላይ ገዢዎች አድርገህ ላስነሣሃቸው
ነገሥታት ገቢ ይሆናል፤
እነርሱ በእኛና በእንስሶቻችን ላይ
ደስ ያሰኛቸውን ነገር ሁሉ ይፈጽማሉ፤
ከዚህም የተነሣ፥ በታላቅ ጭንቀት ላይ እንገኛለን።”
ሕዝቡ የጽሑፍ ስምምነት መፈረሙ
38ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እኛ የጽሑፍ ስምምነት ለማድረግ ወሰንን፤ በስምምነቱም ጽሑፍ ላይ መሪዎቻችን፥ ሌዋውያኖቻችንና ካህናቶቻችን ማኅተማቸውን አኖሩበት።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in

Videos for መጽሐፈ ነህምያ 9