ትንቢተ ናሆም 3
3
1ለነፍሰ ገዳዮች ከተማ፥
ፈጽማ አታላይ ለሆነች፥
በዝርፊያ ለታወቀችና በብዙ ምርኮ ለተሞላች
ለነነዌ ከተማ ወዮላት!
2የአለንጋና የመንኰራኲሮች ድምፅ፥
የፈረስ ግልቢያና የሠረገላ መንጓጓት ይሰማል።
3ፈረሰኞች ወደፊት እየገፉ የሚያብረቀርቅ ሰይፋቸውንና
የሚያብለጨልጭ ጦራቸውን ያነሣሉ፤
ብዙ ሰዎች ስለ ተገደሉ
ሬሳዎች ተከምረዋል፤
ከሬሳውም ብዛት የተነሣ
በዚያ የሚያልፍ ሰው ሁሉ ይደናቀፋል።
4ይህም የሆነው ገደብ በሌለው የአምንዝራይቱ ፍትወት ምክንያት ነው፤
እርስዋ በመተት እመቤትነትና በቊንጅናዋ የምታታልልና
መንግሥታትን በዝሙትዋ፥
ሕዝቦችን በጥንቈላዋ የምትማርክ ነች።
5የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦
“እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቼአለሁ፤
ቀሚስሽን ገልቤ ፊትሽን እሸፍናለሁ፤
ሕዝቦች ራቁትነትሽን፥
መንግሥታትም ኀፍረትሽን ያያሉ።
6የቈሻሻ መጣያ አደርግሻለሁ፤
በንቀት እመለከትሻለሁ፤
ሰው ሁሉ እንዲሳለቅብሽ አደርጋለሁ።
7የሚያይሽ ሁሉ በመሸማቀቅ
‘እነሆ ነነዌ ፈራርሳ ውድማ ሆናለች፤
ማን ያዝንላታል?’ ይላል።
የሚያጽናናትስ እኔ ከወዴት አገኝላታለሁ?”
8ነነዌ ሆይ! አንቺም የውሃ መከላከያ እንዳለሽ ሁሉ በአባይ ወንዝ አጠገብ ከነበረችው፥ ዙሪያዋ በውሃ ከተከበበው፥ የባሕር ውሃም መከላከያዋ ከሆነው ከግብጽ ከተማ ከቴብስ ትበልጫለሽን? 9ወሰን የሌለው ኀይልዋ ከግብጽ ከራስዋና ከኢትዮጵያ ይመጣ ነበር፤ የፉጥና ሊብያ ሰዎችም ተባባሪዎችዋ ነበሩ። 10ይህም ሁሉ ሆኖ የቴብስ ከተማ በጠላት ተይዛ ሕዝቦችዋ ተማርከዋል፤ ሕፃናትዋም በድንጋይ ተፈጥፍጠው በየመንገዱ ወድቀዋል፤ በልዑላኑ ላይ ዕጣ ተጣጣሉ፤ ሹማምንቱንም በሰንሰለት አሰሩአቸው።
11ነነዌ ሆይ! አንቺም ሰክሮ እንደሚንገዳገድ ሰው የምትሆኚበትና ከጠላቶችሽ ፊት ሸሽተሽ መጠጊያ የምትፈልጊበት ጊዜ ይመጣል። 12ምሽግሽ ሁሉ ቀድሞ የደረሰ ፍሬ እንደ ተሸከመ የበለስ ዛፍ ይሆናል፤ እርሱ ተነቅንቆ ፍሬው በተራገፈ ጊዜ በበላተኛ አፍ ውስጥ ይወድቃል። 13ወታደሮችሽ ሁሉ እንደ ሴት ፈሪዎች ሆነዋል፤ የጠረፍሽ በሮች ለጠላቶችሽ ክፍት ሆነዋል፤ መወርወሪያዎቹም እሳት በልቶአቸዋል። 14ጠላቶችሽ ከበው በሚያስጨንቁሽ ጊዜ የምትጠጪውን ውሃ ቀድተሽ አዘጋጂ! ምሽጎችሽን አጠናክሪ! ጭቃ ረግጠሽ የሸክላ መሥሪያ አዘጋጂ! ጡብም ሥሪ።
15በእሳት ትቃጠያለሽ ሕዝብሽም በጦርነት ማለቁ አይቀርም፥ በአንበጣ እንደ ተበላ ሰብል ትጠፊያለሽ፤ ስለዚህ እንደ አንበጣና እንደ ኲብኲባ ተባዙ።
16ነጋዴዎችሽ ከሰማይ ከዋክብት ይበልጥ በዝተዋል፤ ነገር ግን እንደ አንበጣ ምድሪቱን ግጠው በረው ይሄዳሉ። 17ጠባቂዎችሽ እንደ ኲብኲባ፥ ባለ ሥልጣኖችሽ በብርድ ቀን በአጥር ላይ እንደ ሰፈረ የአንበጣ መንጋ ናቸው፤ ፀሐይ ሲወጣ በረው ይሄዳሉ፤ ወዴት እንደሚሄዱ ግን የሚያውቅ የለም።
18የአሦር ንጉሥ ሆይ፥ ጠባቂዎችህ ተኝተዋል፤ ልዑላንህ አንቀላፍተዋል፤ ሕዝብህ በተራራ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሰበስባቸውም የለም። 19ክፉኛ የተጐዳሽ ስለ ሆነ ቊስልሽን ሊፈውስ የሚችል ነገር የለም፤ ማለቂያ ከሌለው ከአንቺ የጭካኔ ድርጊት ያመለጠ ሰው ስለሌለ ስለ አንቺ የሚሰሙ ሁሉ በአንቺ መውደቅ ያጨበጭባሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ናሆም 3: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997