ትንቢተ ናሆም 1
1
በነነዌ ላይ የተገለጠ የእግዚአብሔር ቊጣ
1ስለ ነነዌ ጥፋት ኤልቆሻዊው ናሆም የተናገረው ቃልና ያየው ራእይ የሚከተለው ነው። #ኢሳ. 10፥5-34፤ 14፥24-27፤ ሶፎ. 2፥13-15።
2እግዚአብሔር ቀናተኛ ተበቃይ አምላክ ነው፤
በኀይለኛ ቊጣውም፥ በጠላቶቹ ላይ መዓቱን ያወርዳል።
3እግዚአብሔር ታጋሽና ኀያል ነው፤
ነገር ግን በደለኛውን ሳይቀጣው አያልፍም፤
መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በሞገድ ውስጥ ነው፤
ሰው ሲራመድ ትቢያን እንደሚያስነሣ፥
የእግዚአብሔርም መገለጥ ደመናን ያስከትላል።
4እግዚአብሔር ባሕሩንና ወንዞቹን
ገሥጾ ያደርቃቸዋል።
በባሳንና በቀርሜሎስ የሚገኙ ዕፀዋት ይደርቃሉ፤
የሊባኖስም አበቦች ይጠወልጋሉ።
5በእግዚአብሔር ፊት ተራራዎች ይንቀጠቀጣሉ፤
ኰረብቶችም ይቀልጣሉ፤
በእግዚአብሔር ፊት ምድር ትናወጣለች፤
ዓለምና በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ።
6በእርሱ ኀይለኛ ቊጣ ፊት መቆም የሚችል ማን ነው?
ቊጣውስ እንደ እሳት በነደደ ጊዜ የሚችለው ማነው?
እንደ እሳት የሚያቃጥል ቊጣው በሚወርድበት ጊዜ
አለቶች ተሰነጣጥቀው ይበታተናሉ።
7እግዚአብሔር ቸር ነው፤
በመከራ ጊዜም ጠንካራ መሸሸጊያ ነው፤
በእርሱ የሚተማመኑትን ሁሉ ይንከባከባል።
8ተቃዋሚዎቹን በኀይለኛ ጐርፍ ያጥለቀልቃቸዋል፤
ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።
9እናንተ በእግዚአብሔር ላይ የምታሤሩት ለምንድን ነው?
እርሱ እናንተን እስከ መጨረሻው ይደመስሳችኋል፤
ዳግመኛም በእርሱ ላይ መነሣሣት ከቶ አትችሉም።
10እናንተ ሰካራሞች!
እርስ በርሱ የተያያዘ እሾኽና ድርቆሽ
በእሳት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ፥
እናንተም እንዲሁ ትጠፋላችሁ።
11የነነዌ ሕዝብ ሆይ! በእግዚአብሔር ላይ ሤራ የሚያሤርና ክፉ ምክር የሚመክር ሰው ከመካከላችሁ ተነሥቶአል። 12እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለይሁዳ እንዲህ ይላል፦ “አሦራውያን ኀይለኞችና ቊጥራቸው የበዛ ቢሆንም እንኳ ተደምስሰው እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ሕዝቤ ሆይ! ከዚህ በፊት መከራ ያጸናሁባችሁ ቢሆንም እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን አላደርግባችሁም። 13አሦራውያን በእናንተ ላይ የጫኑትን የጭቈና አገዛዝ አስወግዳለሁ፤ እናንተን ያሰሩበትንም እግር ብረት እሰብራለሁ።”
14እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን የሰጠው ፍርድ እንዲህ የሚል ነው፦ “ከእንግዲህ ወዲህ ስማችሁን የሚያስጠራ ተተኪ ዘር አይኖራችሁም፤ በአማልክታችሁ ቤተ መቅደስ የሚገኙትን የተቀረጹ ምስሎችንና ቀልጠው የተሠሩ ጣዖቶችን አጠፋለሁ፤ እናንተም ዋጋ ቢሶች ስለ ሆናችሁ የመቃብር ጒድጓድ እምስላችኋለሁ።” 15እነሆ መልካም ዜናን የሚያበሥር፥ ሰላምንም የሚያውጅ መልእክተኛ በተራሮች ላይ እየመጣ ነው። የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ክፉዎች ጠላቶችህ ፈጽሞ ስለ ተደመሰሱ ከእንግዲህ ወዲህ አገርህን ከቶ አይወሩአትም! ስለዚህ ዓመት በዓሎችህን በደስታ አክብር! ስእለትህንም ለእግዚአብሔር ስጥ! #ኢሳ. 52፥7።
Currently Selected:
ትንቢተ ናሆም 1: አማ05
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997