YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 4

4
የዘሪው ምሳሌ
(ማቴ. 13፥10-17ሉቃ. 8፥4-8)
1ኢየሱስ እንደገና በባሕሩ አጠገብ ማስተማር ጀመረ። እጅግ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው እርሱ በባሕሩ ላይ በነበረው ጀልባ ገብቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ነበሩ። #ሉቃ. 5፥1-3። 2ብዙ ነገሮችንም በምሳሌ አስተማራቸው፤ ሲያስተምራቸውም እንዲህ አላቸው፦ 3“ስሙ! እነሆ፥ ገበሬው ዘሩን ለመዝራት ወጣ፤ 4ሲዘራ ሳለ አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። 5ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ ቦታ ላይ ወደቀ፤ ቦታውም ብዙ ዐፈር ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ 6ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ የጠለቀ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። 7ሌላው ዘር በእሾኽ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም ባደገ ጊዜ ስላነቀው ያለ ፍሬ ቀረ። 8ሌላው ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለ፤ ቡቃያውም አድጎ ፍሬ ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም መቶ አፈራ።”
9ቀጥሎም ኢየሱስ፦ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” አለ።
ኢየሱስ ስለምን በምሳሌ ይናገር እንደ ነበረ
(ማቴ. 13፥10-17ሉቃ. 8፥9-10)
10ኢየሱስ ብቻውን በሆነ ጊዜ ይከተሉት የነበሩ ሰዎችና ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ስለ ምሳሌዎቹ ትርጒም ጠየቁት። 11እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ለእናንተ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ በውጪ ላሉት ግን ሁሉ ነገር በምሳሌ ይነገራቸዋል። 12ይህም የሚሆነው፥
‘እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው
ኃጢአታቸው ይቅር እንዳይባልላቸው፥
ማየትን እያዩ ልብ አያደርጉም፤
መስማትን እየሰሙ አያስተውሉም፤’ ” በተባለው መሠረት ነው። #ኢሳ. 6፥9-10።
የዘሪው ምሳሌ ትርጒም
(ማቴ. 13፥18-23ሉቃ. 8፥11-15)
13ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተም ይህ ምሳሌ አይገባችሁምን? ታዲያ፥ ሌሎችን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? 14ዘሪው ቃልን ይዘራል፤ 15ቃሉ በተዘራ ጊዜ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው ቃሉን በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልባቸው የተዘራውን ቃል የሚወስድባቸውን ሰዎች ነው። 16እንዲሁም በጭንጫማ ቦታ ላይ የተዘራው የሚያመለክተው ቃሉን ሲሰሙ ወዲያው በደስታ የሚቀበሉትን ሰዎች ነው፤ 17ግን እነርሱ ለጊዜው ነው እንጂ በልባቸው ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቃሉ ምክንያት ችግር ወይም ስደት ቢደርስባቸው ወዲያውኑ ተሰናክለው ይወድቃሉ። 18በእሾኽ መካከል የተዘራው ደግሞ የሚያመለክተው ቃሉን የሚሰሙትን ሰዎች ነው፤ 19ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብ፥ የሀብት ፍቅርና ሌላውም ከንቱ ምኞት ወደ ልባቸው ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። 20በመልካም መሬት የተዘራው ግን የሚያመለክተው ቃሉን ሰምተው በማስተዋል የሚቀበሉትን ሰዎች ነው። እንዲህ ዐይነቱ አንዱ ሠላሳ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም መቶ ፍሬ ያፈራል።
መብራት የሚበራው ብርሃን እንዲሰጥ መሆኑ
(ሉቃ. 8፥16-18)
21“ሰው መብራትን አብርቶ በእንቅብ ውስጥ ወይም በአልጋ ሥር ያስቀምጠዋልን? የሚያስቀምጠው፥ ብርሃኑ በሚታይበት በመቅረዝ ላይ አይደለምን? #ማቴ. 5፥15፤ ሉቃ. 11፥33። 22እንዲሁም የተሸሸገ ሳይገለጥ፥ የተሰወረም ሳይታወቅ አይቀርም። #ማቴ. 10፥26፤ ሉቃ. 12፥2። 23እንግዲህ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”
24እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምትሰሙት ነገር ተጠንቀቁ! በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ለእናንተም ይሰፈርላችኋል፤ በይበልጥም ይጨመርላችኋል። #ማቴ. 7፥2፤ ሉቃ. 6፥38። 25ላለው ይሰጠዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።” #ማቴ. 13፥12፤ 25፥29፤ ሉቃ. 19፥26።
የዘር ዕድገት ምሳሌ
26ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ዘር የሚዘራውን ሰው ትመስላለች። 27ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀንም ይነቃል፤ እንዴት እንደ ሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል፤ ያድጋልም። 28ምድሪቱም በገዛ ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፥ ቀጥሎም ዛላውን ታሳያለች፤ በኋላም በዛላው ፍሬ ይገኛል። 29ሰብሉም በደረሰ ጊዜ መከር በመሆኑ ሰውየው ወዲያውኑ ማጭድ ያዘጋጃል።” #ኢዩ. 3፥13።
የሰናፍጭ ዘር ምሳሌ
(ማቴ. 13፥31-34ሉቃ. 13፥18-19)
30ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር እናነጻጽራታለን? ወይስ በምን ምሳሌ እንገልጻታለን? 31የሰናፍጭን ዘር ትመስላለች፤ እርስዋ ስትዘራ በምድር ላይ ካለው ዘር ሁሉ ያነሰች ናት። 32ከተዘራች በኋላ ግን አድጋ ከአትክልት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በሥርዋ ጎጆ ሠርተው መጠለል እስኪችሉ ድረስ ታላላቅ ቅርንጫፎችን ታወጣለች።”
33ኢየሱስም ሰዎች ማስተዋል በሚችሉበት መጠን፥ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ቃሉን ይነግራቸው ነበር። 34ያለ ምሳሌም አያስተምራቸውም ነበር፤ ብቻቸውን ሲሆኑ ግን ሁሉን ነገር ለደቀ መዛሙርቱ ያስረዳቸው ነበር።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ ማድረጉ
(ማቴ. 8፥23-27ሉቃ. 8፥22-25)
35በዚያኑ ቀን ማታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው። 36ከሕዝቡም ተለይተው ተሳፍሮበት በነበረው ጀልባ ኢየሱስን ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎችም ጀልባዎች አብረው ነበሩ። 37ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ተነሥቶ ውሃው በጀልባው እስኪሞላ ድረስ ማዕበሉ ጀልባውን ይመታ ጀመር። 38በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፥ በጀልባው በኋለኛው ክፍል ትራስ ተንተርሶ ተኝቶ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ቀሰቀሱትና “መምህር ሆይ! ስንጠፋ አይገድህምን?” አሉት።
39እርሱም ነቅቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም “ጸጥ በል!” አለው፤ ነፋሱ ተወ፤ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። 40ኢየሱስም፦ “እንዲህ የምትፈሩት ለምንድን ነው? እንዴትስ እምነት የላችሁም?” አላቸው።
41እነርሱም በጣም ፈርተው፥ እርስ በርሳቸው “ኧረ ለመሆኑ፥ ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in