YouVersion Logo
Search Icon

የማርቆስ ወንጌል 13

13
ሰለ ቤተ መቅደስ መፍረስ የኢየሱስ ትንቢት
(ማቴ. 24፥1-2ሉቃ. 21፥5-6)
1ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ሳለ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “መምህር ሆይ! እነዚህን ድንጋዮችና ሕንጻዎች ተመልከት፤ የሚያስደንቁ ናቸው!” 2ኢየሱስም “እነዚህን ትልልቅ ሕንጻዎች ታያለህን? እነዚህ ድንጋዮች ሁሉ ይፈርሳሉ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ የሚቀር የለም፤” ብሎ መለሰለት።
የዘመኑ መጨረሻ ምልክቶች
(ማቴ. 24፥3-14ሉቃ. 21፥7-19)
3ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፥ ያዕቆብ፥ ዮሐንስና፥ እንድርያስ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው 4“ይህ ነገር የሚሆነው መቼ ነው? ይህስ ሁሉ ሊፈጸም ሲቃረብ ምልክቱ ምንድን ነው? እስቲ ንገረን” ሲሉ ጠየቁት።
5ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤ 6ብዙዎች ‘እኔ መሲሕ ነኝ!’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙ ሰዎችንም ያሳስታሉ፤ 7በአቅራቢያችሁ ጦርነት ሲደረግና በሩቅም የጦርነትን ወሬ ስትሰሙ አትደንግጡ፤ ይህ ሁሉ ሊሆን ግድ ነው፤ ይሁን እንጂ መጨረሻው ገና ነው። 8ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ጦርነት ያነሣል፤ በየስፍራው የምድር መናወጥና ራብ ይሆናል፤ ይህ ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቅ መጀመሪያ ነው።
9“እናንተም ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ሰዎች ለፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በየምኲራቡም ይገርፉአችኋል፤ ምስክር እንድትሆኑኝ በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ለፍርድ ትቆማላችሁ። #ማቴ. 10፥17-20። 10ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ወንጌል ለዓለም ሕዝብ ሁሉ መዳረስ ይገባዋል። 11ሰዎች ይዘው ወደ ፍርድ ሲያቀርቡአችሁ፥ ‘ምን እንናገር ይሆን?’ በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁም። ስለዚህ በዚያን ሰዓት የሚሰጣችሁን ብቻ ተናገሩ። 12ወንድም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ ይገድሉአቸዋልም። 13ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ በትዕግሥት የሚጸና ግን ይድናል። #ማቴ. 10፥22።
አሠቃቂው መከራ
(ማቴ. 24፥15-28ሉቃ. 21፥20-24)
14“ደግሞ መገኘት በማይገባው ስፍራ የሚያረክሰውን አጸያፊ ነገር ታያላችሁ፤ ይህንንም አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ምድር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ። #ዳን. 9፥27፤ 11፥31፤ 12፥11። 15በቤት ጣራ ላይ ያለ ወደ ቤቱ ወርዶ ከቤቱ አንዳች ነገር ለመውሰድ ጊዜ አያጥፋ፤ #ሉቃ. 17፥31። 16በእርሻም ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ ወደ ኋላው አይመለስ። 17በዚያን ጊዜ ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! 18ይህ ሁሉ በክረምት ጊዜ እንዳይሆን ጸልዩ። 19በዚያን ወራት እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ መከራ ይሆናል፤ ወደ ፊትም እሱን የሚመስል ጭንቀት ከቶ አይደርስም። #ዳን. 12፥1፤ ራዕ. 7፥14። 20ጌታ እነዚያን ቀኖች ባያሳጥርማ ኖሮ ማንም መዳን ባልቻለም ነበር፤ ነገር ግን ለተመረጡት ሰዎች ሲባል እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ።
21“እንግዲህ ማንም ቢሆን ‘መሲሕ ይኸው እዚህ ነው!’ ወይም ‘ያው እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። 22ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይመጣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ለማሳሳት ተአምራትና ድንቅ ነገሮችን ያደርጋሉ። 23ሁሉን ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁና እንግዲህ ተጠንቀቁ!
የክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት
(ማቴ. 24፥29-31ሉቃ. 21፥25-28) #ኢሳ. 13፥10ሕዝ. 32፥7ኢዩ. 2፥10313፥15ራዕ. 6፥12
24“በዚያን ጊዜ፥ ከዚያ ሁሉ መከራ በኋላ፥ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ 25ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በሰማይ ያሉ ኀይሎችም ይናወጣሉ። #ኢሳ. 34፥4፤ ኢዩ. 2፥10፤ ራዕ. 6፥13። 26ከዚያም በኋላ የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ይታያል፤ #ዳን. 7፥13፤ ራዕ. 1፥7። 27መላእክቱንም ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም አቅጣጫ ሄደው ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የሚገኙትን፥ ለእርሱ የተመረጡትን ሰዎች ይሰበስባሉ።
የጌታን መምጫ የምታመለክት የበለስ ዛፍ ምሳሌ
(ማቴ. 24፥32-35ሉቃ. 21፥29-33)
28“የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። #13፥28 በጋ፦ ይህ ገለጻ የሚያመለክተው፥ በእነርሱ አገር ዛፎች የሚያቈጠቊጡትና ቅጠሎች የሚለመልሙት በበጋ መሆኑን ነው። 29እንዲሁም እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ፤ 30በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ትውልድ ከማለፉ በፊት ይህ ሁሉ ይፈጸማል። 31ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ጸንቶ ይኖራል።
ጌታ የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ማንም አያውቅም
(ማቴ. 24፥36-44)
32“ነገር ግን ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ የሰማይ መላእክትም አያውቁም፤ ወልድም አያውቅም። #ማቴ. 24፥36። 33ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ። 34ይህም፥ ቤቱን ትቶ ወደ ሩቅ አገር የሄደውን ሰው ይመስላል፤ እርሱም እያንዳንዱን አገልጋይ በልዩ ልዩ የሥራ ኀላፊነት ላይ መደበ፤ ዘበኛውንም ተግቶ እንዲጠብቅ አዘዘው። #ሉቃ. 12፥36-38። 35ስለዚህ የቤቱ ጌታ የሚመጣበትን ጊዜ አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ምናልባትም ወደ ማታ፥ ወይም በእኩለ ሌሊት፥ ወይም ዶሮ ሲጮኽ፥ ወይም ጠዋት በማለዳ ይመጣ ይሆናል፤ 36በድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ትጉ።
37“ለእናንተ እንደ ነገርኳችሁ ለሌሎችም ሁሉ ትጉ! እላለሁ።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in