YouVersion Logo
Search Icon

የማቴዎስ ወንጌል 10

10
ስለ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት
(ማር. 3፥13-19ሉቃ. 6፥12-16)
1ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያስወጡ፥ በሽታንና ደዌን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። 2የዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ዝርዝር፥ እንደሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፥ 3ፊልጶስ፥ በርቶሎሜዎስ፥ ቶማስ፥ ቀራጩ ማቴዎስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ 4ቀናኢው ስምዖን፥ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። #10፥4 ቀናኢ፦ ለስምዖን ይህ ቅጽል የተሰጠው፥ አንዳንድ ተርጓሚዎች ለሃይማኖቱ ቀናተኛ ስለ ነበረ ነው ሲሉ፥ ሌሎች ደግሞ የአንድ የነጻ አውጪ ድርጅት አባል ነበር ይላሉ። #10፥4 አስቆሮቱ፦ በዚህ ቃል ላይ ሁለት አስተያየቶች አሉ። አንዱ አስተያየት፥ ከቦታ ወይም ከሀገር ጋር ሲያያይዘው ሌላው ወገን ደግሞ ይሁዳን ውሸታም ወይም አታላይ ብሎ ለመስደብ የተሰጠ ቅጽል ነው ይላል።
ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ለማስተማር እንደ ተላኩ
(ማር. 6፥7-13ሉቃ. 9፥1-6)
5ኢየሱስ እነዚህን ዐሥራ ሁለት ሐዋርያት ላካቸው፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ 6ይልቅስ እንደ በጎች ወደ ጠፉት ወደ እስራኤል ሕዝቦች ሂዱ። 7ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማይ ቀርባለች!’ እያላችሁ ስበኩ። #ሉቃ. 10፥4-12። 8በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ። 9ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በኪሳችሁ አትያዙ። 10ለሠራተኛ ምግቡ የሚገባው ስለ ሆነ ለመንገዳችሁ ከረጢት፥ ትርፍ እጀ ጠባብ፥ ትርፍ ጫማ፥ በትርም አትያዙ። #1ቆሮ. 9፥14፤ 1ጢሞ. 5፥18። 11በምትገቡበት ከተማ ወይም መንደር፥ ተገቢ የሆነ ሰው ማን እንደ ሆነ መርምሩ፤ ያንንም ስፍራ ለቃችሁ እስክትወጡ ድረስ ከእርሱ ጋር ቈዩ። 12ወደ ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ 13ቤቱ ለሰላማችሁ ተገቢ ቢሆን ሰላማችሁ ይድረሰው፤ ተገቢ ባይሆን ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ። 14ማንም ሰው የማይቀበላችሁ ወይም ቃላችሁን የማይሰማ ቢሆን ያንን ቤት ወይም ከተማ ለቃችሁ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ። #ሐ.ሥ. 13፥51። 15በእውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ ሰዎች ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። #ማቴ. 11፥24፤ ዘፍ. 19፥24-28።
ከጌታ መምጣት በፊት ስደትና መከራ እንደሚሆን
(ማር. 13፥3-13ሉቃ. 21፥12-17)
16“እነሆ! እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች፥ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ። #ሉቃ. 10፥3። 17ሰዎች ወደ ፍርድ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ በየምኲራባቸውም ይገርፉአችኋል፤ ስለዚህ ከሰዎች ተጠንቀቁ። #ማር. 13፥9-11፤ ሉቃ. 12፥11-12፤ 21፥12-15። 18በእኔ ምክንያት፥ ወደ ገዢዎችና ወደ ነገሥታት ለፍርድ ስለምትወሰዱ በእነርሱና በአሕዛብ ፊት ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤ 19ሰዎች ወደ ፍርድ ሸንጎ ሲያቀርቡአችሁ የምትናገሩት ነገር በዚያን ሰዓት ስለሚሰጣችሁ፥ ‘እንዴት ወይም ምን እንናገራለን?’ ብላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። 20በእናንተ ውስጥ ዐድሮ የሚናገር የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁም። #ማር. 13፥12፤ ሉቃ. 21፥16። 21ሰው የገዛ ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ እንዲሁም አባት የገዛ ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ በጠላትነት ይነሣሉ፤ ለሞትም አሳልፈው ይሰጡአቸዋል። 22በእኔ ምክንያት በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻው ጸንቶ የሚቆም ይድናል። #ማቴ. 24፥9፤13፤ ማር. 13፥13፤ ሉቃ. 21፥17። 23በአንድ ከተማ መከራ ሲያበዙባችሁ፥ ወደ ሌላው ሽሹ፤ በእውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተሞች ሁሉ አታዳርሱም። 24ተማሪ ከአስተማሪው አይበልጥም፤ አገልጋይም ከጌታው አይበልጥም። #ሉቃ. 6፥40፤ ዮሐ. 13፥16፤ 15፥20። 25ስለዚህ ተማሪ እንደአስተማሪው፥ አገልጋይም እንደ ጌታው ከሆነ ይበቃዋል። የቤቱን ጌታ ‘ብዔልዜቡል’ ብለው ከጠሩት ቤተሰቦቹንማ ከዚህ በከፋ ስም እንዴት አይጠሩአቸውም! #ማቴ. 9፥34፤ 12፥24፤ ማር. 3፥2፤ ሉቃ. 11፥15።
ማንን መፍራት እንደሚገባ
(ሉቃ. 12፥4-7)
26“እንግዲህ ሰዎችን አትፍሩ፤ የተሸፈነ መገለጡ አይቀርም፤ የተሰወረም መታወቁ አይቀርም። #ማር. 4፥22፤ ሉቃ. 8፥17። 27ስለዚህ እኔ በጨለማ የምነግራችሁን፥ እናንተ በብርሃን ተናገሩት፤ በሹክሹክታ የሰማችሁትንም በከፍተኛ ቦታ ላይ መጥታችሁ በይፋ አስተምሩ። 28ሥጋን ከመግደል አልፈው ነፍስን መግደል የማይችሉትን ሰዎች አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን አምላክ ፍሩ። 29ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ፥ የሰማይ አባታችሁ ሳይፈቅድ፥ አንዲቱ ድንቢጥ እንኳ በምድር ላይ ወድቃ አትቀርም። 30የእናንተ ግን የራስ ጠጒራችሁ እንኳ የተቈጠረ ነው። 31እንግዲህ እናንተ ግን ከብዙ ድንቢጦች እጅግ ስለምትበልጡ ከቶ አትፍሩ።
ስለ ክርስቶስ መመስከር የሚገባ መሆኑ
(ሉቃ. 12፥8-9)
32“በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ። 33በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ግን እኔም በሰማይ አባቴ ፊት እክደዋለሁ። #2ጢሞ. 2፥12። 34እኔ የመጣሁት፥ ሰላምን በምድር ላይ ለማምጣት አይምሰላችሁ፤ እኔ ጦርነትን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም። 35እኔ የመጣሁት፥ ወንድ ልጅን በአባቱ ላይ፥ ሴት ልጅን በእናትዋ ላይ፥ ምራትን በዐማትዋ ላይ፥ በጠላትነት ለማስነሣት ነው። 36ስለዚህ የሰው ጠላቶቹ፥ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ። #ሚክ. 7፥6። 37ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ፥ የእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ፥ የእኔ ሊሆን አይገባውም። 38የገዛ ራሱን መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ሰው የእኔ ሊሆን አይገባውም። #ማቴ. 16፥24፤ ማር. 8፥34፤ ሉቃ. 9፥23። 39ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። #ማቴ. 16፥25፤ ማር. 8፥35፤ ሉቃ. 9፥24፤ 17፥33፤ ዮሐ. 12፥25። 40እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን አብን ይቀበላል። #ማር. 9፥37፤ ሉቃ. 9፥48፤ 10፥16፤ ዮሐ. 13፥20። 41ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል። 42በእውነት እላችኋለሁ፤ የእኔ ደቀ መዝሙር በመሆኑ፥ ከነዚህ ታናናሾች ለአንዱ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ እንኳ የሚሰጥ ሰው ዋጋውን አያጣም።”

Highlight

Share

Copy

None

Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in